ኢህአዴግ በአዲስ አበባ መጪውን ምርጫ 99 በመቶ ለማሸነፍ የሚያስቸለውን እንቅስቃሴ ጀመረ

ሰኔ ፲፱ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ መንግሥት በመጪው ዓመት የሚካሄደውን የአዲስ አበባ እና የክልሎች የአካባቢ ምርጫ በሞኖፖል ጠርንፎ ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ከአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት የዜና ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡

በየክረምቱ በአዲስ አበባ እና ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች አዳሪ የክረምት ኮርስ ስልጠና የሚወስዱ መምህራን ዓመታዊ የትምህርት ክፈለ-ጊዜያቸው ዘንድሮ ሊታጠፍ እንደሚችል፣ በምትኩ ኢህአዴግ የሚያካሂደው ሀገራዊ ንቅናቄ በዩኒቨርስቲዎች፣ በትምህርት ቤት ተቋማትና በወረዳ አዳራሾች በስፋት በመላ ሀገሪቱ ለማካሄድ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።

ለዚህም ቅድመ ዝግጅት ይሆን ዘንድ በዘንድሮው የትምህርት መርሃ-ግብር በየዩኒቨርስቲዎች፣ የመሰናዶ እና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዓመታዊ የትምህርት መርሃ- ግብራቸውን በአግባቡ ሳያጠናቅቁ ተማሪዎችን ለፈተና እንዲያስቀምጡና እንዲያሰናብቱ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል መመሪያ ያወረደው የኢህአዴግ መንግሥት ፣ አሁን ሀገራዊ የምርጫ ንቅናቄ ለመፍጠር ዝግጅቱን በማቀላጠፍ ላይ ይገኛል በማለት ምንጮቻችን አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል የሚገኙ መመህራን ደግሞ የትምህርቱን ጊዜ ከአንድ ወር በፊት አጠናቀው ተማሪዎችን እንዲበትኑ የተሰጣቸው ጊዜ እንደገና መቀየሩን መምሀራን ለኢሳት ገልጠዋል።

ቀደም ብሎ ከክልሉ የተላከው ደብዳቤ  ማንኛውም መምህር ፈተናው አጠናቆ ውጤቱን ለሰኔ 19 ቀን 2004 ዓም እንዲያስረክብ የሚል ነበር። በዚህም መሰረት መምህራን ትምህርቱን በአጣዳፊ ሁኔታ በመጨረስ ተማሪዎች ከመደበኛው ጊዜ አንድ ወር በፊት ፈተና እንዲወስዱ አድርገዋል። ተማረዎችም ቅሬታቸውን በመያዝ ፈተናቸውን ወስደው ከጨረሱ በሁዋላ እንደገና ከክልሉ የመጣ ደብዳቤ መጀመሪያ የተላከው ደብዳቤ ተሽሮ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመጀመሪያ በተያዘው እቅድ መሰረት እንዲያጠናቅቁ የሚል መመሪያ አዝሏል። ይሁን እንጅ ደብዳቤው የተላከው ተማሪዎች የሰሚስተሩን ፈተና ጨርሰው በተበተኑበት ሰአት በመሆኑ ምንም ለማድረግ ሳይቻል ቀርቷል። መምህራን በተደጋጋሚ የሚታየው የመንግስት እርምጃ ሆን ተብሎ የአንድ አካባቢን ትውልድ ለመግደል የታለመ ነው በማለት ለኢሳት ገልጠዋል።

የአማራ ክልላዊ መንግስት በተማሪዎች ህይወት ላይ ቁማር የሚጫወት ህግ ማውጣቱን መምህራንን እያበሳጨ መሆኑን ነው መምህራን የሚገልጡት።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide