ሚያዝያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ነጻ ፕሬሱን በማዋከብ፣ በማሳደድ፣ በማሰር ከሚያደርገው ቀጥተኛ ጥቃት በተጨማሪ ስልታዊ ጥቃትን በተጠናከረ መልኩ ስራ ላይ እያዋለ ነው።
በነገው ዕለት የሚከበረው የዓለም የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ ታስቦ የሚውለው የፕሬሱ ስልታዊ አፈና በተጠናከረበት ወቅት መሆኑም ያነጋገርናቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ምንም ዓይነት ትችትና የተለየ አስተያየት ለመስማት ዝግጁ ያልሆነው የኢህአዴግ መንግስት ከእስርና ከስደት የተረፉ፣ ጥቂት በሕትመት ላይ የሚገኙ የግሉ ፕሬሶችን ከብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ጋር በመቀናጀት ጋዜጦች መውጣት ካለባቸው ቀናት እስከሶስት ቀናት
እንዲዘገዩና እንዲወጡ በማድረግ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እንዲገቡ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ማተሚያ ቤቱ በየጊዜው ከሚያቀርበው የማሽን ብልሽት ምክንያት በተጨማሪ ሌሎች ምክንያቶችን እየሰጠ ጋዜጦቹን በማዘግየቱ ጋዜጦቹ የገበያ ችግር የገጠማቸው ከመሆኑም በላይ ማስታወቂያ አስነጋሪዎች በውሉ መሰረት በቀኑ ባለመውጣቱ አንከፍልም የሚል
መከራከሪያ እያቀረቡ መሆናቸው የጋዜጦቹ ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡
በሌላ በኩልም የማተሚያ ባለቤቶችን በማስፈራራት የሚያትሙዋቸውን መጽሔቶች እንዲያቋርጡ ሲደረግ የቆየ ሲሆን አሳታሚዎቹ አቤቱታና ቅሬታ ሲያቀርቡ መንግስት ጉዳዩን እንደማያውቅ ሆኖ እንደሚቀርብ ነገርግን ምንም ዓይነት መፍትሔ እንደማይሰጥ ጠቅሰዋል፡፡
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በተጨማሪም ፕሬሱን በቀላሉ ለማጥቃት ይመቸኛል ብሎ በትጋት እያከናወነ ከሚገኘው እርምጃዎች መካከል ካለፈው አንድ ወር ወዲህ በፕሬሶቹ ላይ የጀመረው የታክስ ኦዲት ምርመራ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዘዴ የሚፈለግባችሁን የታክስና ግብር አልከፈላችሁም የተባሉት የቆንጆ መጽሔት እና የፍቱን መጽሔት አሳታሚዎች እስርን በመስጋት ባለፈው ሳምንት ሥራቸውን በመተው ሀገር ጥለው ተሰደዋል።
በሚቀጥለው ግንቦት ወር የሚካሄደውን ምርጫ አስቀድሞ ጥርጊያ መንገድ ለማመቻቸት ባለፈው ዓመት ነሃሴ ወር ከ6 በላይ ፕሬሶች በፖለቲካ ውሳኔ በጅምላ እንዲከሰሱ የተደረገ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ከ15 በላይ ጋዜጠኞች ሀገር ጥለው መሰደዳቸው የሚታወስ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅትም ሰሞኑን ፍትህ ሳያገኙ በእስር ላይ አንድ ዓመት ያስቆጠሩትን የዞን 9 ጦማርያን በተጨማሪ አራት ጋዜጠኞች በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ከፕሬስ ጋር በተያያዘ የታሰረው አንድ ጋዜጠኛ ማለትም ተመስገን ደሳለኝ ብቻ ሲሆን ቀሪዎቹ በሽብር
ድርጊት የተጠረጠሩ እንጂ በሙያቸው የታሰሩ አለመሆናቸውን የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በቅርቡ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ይበሉ እንጂ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና በርካታ ኢትዮጵያዊያን
ጋዜጠኞቹ
በሙያቸው ምክንያት መታሰራቸውን ያምናሉ፡፡
በየዓመቱ ሜይ 3 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፉ የፕሬስ ቀን በነገው ዕለት የሚከበር ሲሆን ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ ፕሬስ ፍሪደም 2015 ሪፖርት መሰረት የፕሬስ ነጻነትን በማረጋገጥ ረገድ ኢትዮጵያ ከ180 ሀገራት 142 ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡