መስከረም ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ህገመንግስቱ የጸደቀበትን ህዳር 29 ቀን «የብሔር ብሔረሰቦች ቀን» በሚል በየዓመቱ ሲያከብረው የቆየው ኢህአዴግ ዘንድሮ 20ኛውን
ዓመት በተለየ ድምቅት በማክበር ሕዝቦች በሕገመንግስቱ የተረጋገጡላቸውን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አተገባበር እንከን አልባ እንደነበሩ በማጉላት በመጪው ግንቦት ወር ይካሄዳል
ተብሎ በሚገመተው ምርጫ ላይ ከፍተኛ ድል ለማግኘት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ለፌዴሬሽን ምክርቤት ቅርበት ያላቸው ወገኖች ገልጸዋል፡፡
ኢህአዴግ ባለፉት 20 ዓመታት በሕገመንግስቱ መሠረት ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንደተመለሱ ከመግለጽ ባለፈ የሚቀናቀኑትን ኃይሎች እና ጋዜጠኞች ሕገመንግስታዊ
ሥርዓትን ጥሰዋል በሚል በተደጋጋሚ በመክሰስ ማስቀጣቱን አለማቀፍና የአገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ጠባቂ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።
ኢህአዴግ ሲፈልግ ሕገመንግስቱን አክባሪና አስከባሪ፣ ሳይፈልግ ደግሞ የሚጥስ በሆነበት በዚህ ወቅት የህገመንግስቱ የጸደቀበት 20ኛ ዓመት በፈንጠዝያ ለማክበር ማሰቡ በራሱ የሚያስገርም
ነው በማለት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የህግ ምሁርን ለአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ገልጸዋል።
እኝሁ ምሁር በአሁኑ ወቅት በሕጋዊ መንገድ ሕገመንግስቱ በሚፈቅደው መሠረት ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብሰባ አካሂደው ከአባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው
ጋር እንኳን ለመገናኘትና ሃሳብ ለመለዋወጥ የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን፣ በተደጋጋሚ የአደባባይ ተቃውሞዎችን ለማካሄድ የመረጡዋቸውን ቦታዎች ከመከልከል
ጀምሮ ሰልፍ አስተባባሪዎችን እንዲሁም ወደፊት ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ የተባሉ አመራሮችን እስከማሰርና ማሳደድ ደረጃ የሚደርስ እርምጃ መውሰዱ ለራሱ ሕገመንግስት የሚገዛ ኃይል
አለመሆኑን በተጨባጭ ያረጋገጠ አድርጎታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሕገመንገስቱ መሠረት የተቋቋሙ የግል ፕሬሶችም እሱ በሚፈልገው መንገድ ባለመንቀሳቀሳቸው ብቻ እንደአፍራሽ፣ ጸረ ኢትዮጵያ ፣ጸረ ልማት ሓይሎች እንዲታዩ ሌት ተቀን በቁጥጥሩ ስር
ባሉ መገናኛ ብዙሃን ከማስወራት አልፎ በአንድ ጊዜ በርካታ መጽሔቶች እና ጋዜጦች ላይ ክስ በመመስረት ጋዜጠኞች ሳይወዱ በግድ ሀገር ጥለው በብዛት እንዲሰደዱ ምክንያት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ከፕሬሶቹም አልፎ የኢንተርኔት ድረገጾችን በማፈን፣ ብሎገሮችን በማሰር የተለየ ሃሳብ እንዳይንጸባረቅ ገዥው ፓርቲ በርትቶ በሚሰራበት በዚህ ወቅት የህገመንግስት 20ኛ ዓመት ለማክበር ሽርጉድ
ማለት ቀልድ ነው ሲሊም አክለዋል፡፡
የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዳር 29 ቀን የሚከበር ሲሆን ይህንኑ የበዓል ዝግጅት ለማየት የተመረጡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶች፣ ጋዜጠኞች የፌዴሬሽን
ምክርቤት አስተባባሪነት በዛሬው ዕለት ለሁለት ሳምንት ጉብኝት ወደስፍራው አቅንተዋል፡፡
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ያለበቂ የህዝብ ተሳትፎ ያረቀቀው ሕገመንግስት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም መጽደቁ ይታወሳል፡፡
አምና በጅጅጋ ተደርጎ በነበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል። አብዛኛውን ዝግጅቶች የሚያዘጋጁት ከህወሃት ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት ያላቸው የንግድ ድርጅቶች
ሲሆኑ፣ በአሉ ለእነዚህ ድርጀቶች መክበሪያና በተዘዋዋሪ መልኩ የመንግስትን ገንዘብ ወደ ህወሃት ባለስልጣናትና ሸሪኮቻቸው ማስተላለፊያ መሆኑን ይናገራሉ።
በ2006 ዓም ገዢው ፓርቲ ለተለያዩ የህዝብ ግንኙነት ስራዎች 1 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ አውጥቷል።