”ኢህአዴግ ሕዝቦች በአንድ ድምፅ ሲናገሩና ሲሰበሰቡ አይወድም” ሲል የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ሊቀ-መንበር ወጣት ሀብታሙ አያሌው ገለጸ

መስከረም ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባለራዕይ የወጣቶች ማህበር ባለፈው ዓመት ጥር ወር ነው በኢትዮጵያ በበጎ አድራጎት ማኅበራት ምዝገባ ኤጀንሲ የተመዘገበው ።

ማህበሩ፤የቀድሞው የወጣቶች ፌዴሬሽን አመራር የነበረውና ከኢህአዴግ ጋር ለረጅም ጊዜ የሠራው አቶ ሀብታሙ ከኢህአዴግ በመውጣትና ሌሎች ወጣቶችን በማስተባበር ያቋቋመው  ነፃ የብዙኃን ማኅበር ነው።

የማኅበሩ ለቀመንበር ወጣት ሀብታሙ እንደሚለው ፤ ባለራዕይ የወጣቶች ማህበር  በህግ ጥላ ስር የሚንቀሳቀስ ቢሆንም፤በአዲስ አበባ ከተማ በሕዝብ መገልገያ ተቋማት ውስጥ ስብሰባ ማካሄድ አልቻለም።

ሳምንታዊው ሰንደቅ ሊቀመንበሩን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ባለፈው እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሊደረግ የነበረው የባለራዕይ ወጣቶች ም/ቤት ሰብስባ በቀጥታ የኢህአዴግ ካድሬዎች በፈጠሩት እንቅፋት በመደናቀፉ፤ ወጣቶቹ አመቺ ባልሆነ ሁኔታ በማኅበሩ ጽ/ቤት ለመሰብሰብ ተገደዋል።
ቀደም ሲል በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከአንድም ሁለት ጊዜ የማኅበሩ ስብሰባ በፀጥታ ኃይሎች መበተኑን ያስታወሰው የማህበሩ ሊቀመንበር፤ ማኅበሩ ነፃ ሆኖ የኢትዮጵያን አንድነት እንዳይሰብክ- ኢህአዴግ በካድሬዎቹ አማካኝነት ሕገ-መንግስቱን በጠራራ ፀሐይ በመጣስና የፀጥታ ኃይሎችን በማስተባበር ጭምር እያፈነው ነው ሲል አማሯል።

ጋዜጣው ምንጮቹን በመጥቀስ  እንዳለው፤ወጣት  ሀብታሙና አጋሮቹ ያቋቋሙት ማኅበር ዓላማዎች ኢህአዴግ ከሚመራባቸው የፖለቲካ ፍልስፍና  ጋር የተቃረኑ ከመሆናቸው  ጋር ተያይዞ በማህበሩ እና በኢህአዴግ ካድሬዎች መካከል   ጥላቻ ተፈጥሯል።
ወጣት ሀብታሙ፦<ማኅበሩ የማንም ፖለቲካ ድርጅት አይደግፍምም አይቃወምምም> ይላል።

ሆኖም  የኢትዮጵያን አንድነት በተመለከተ ለሁሉም ፓርቲዎች <የአብረን እንስራ> ጥሪ አስተላልፈው ከአብዛኛዎቹ ፓርቲዎች በጎ ምላሽ ሲያገኙ፤ በኢህአዴግ በኩል ግን ምላሽ አለማግኘታቸውን አመልክቷል።
<ማኅበሩ ወጣቶችን አደራጅቶ ለብሔራዊ መግባባትና ለኢትዮጵያ አንድነት ይሰራል> ያለው የማህበሩ ሊቀመንበር ፤ የኢህአዴግ ካድሬዎች ግን በተቀነባበረ መንገድ የማኅበሩን አካሄድ እየጎዱብን ነው ሲል ተናግሯል።
“እኛ በእርግጠኝነት የሀገር ደህንነት ስጋት አይደለንም!በመሆኑም የፀጥታ ኃይሎች- በኢህአዴግ ካድሬዎች እየተመሩ ስብሰባችንን ከማደናቀፍ ይቆጠቡ> ሲልም ጠይቋል-የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ሊቀ-መንበር ወጣት ሀብታሙ።

“እኛ ለስልጣን አንወዳደርም” ያለው ሊቀመንበሩ፤  <የስብሰባ ክልከላው የሚመነጨው ኢህአዴግ ሁልጊዜ በስጋት ውስጥ ያለ ፓርቲ በመሆኑ ነው> ብሏል።
አክሎም፦“ኢህአዴግ ሕዝቦች በአንድ ድምፅ ሲናገሩና ሲሰበሰቡ አይወድም፤ ከቁጥጥሩ ውጪ የሆኑ ኃይሎችን በኃይል ይቆጣጠራል”ብሏልም።

ገዥው ፓርቲ የሕዝቡን ነፃነት ማክበርና ለሕገ-መንግስቱ የበላይነት ሊገዛ ይገባል ሲልም  አሣስቧል።

ስለጉዳዩ የተጠየቁት አንድ ስማቸውን ያልጠቀሱ የኢህአዴግ ባለስልጣን፤ ማህበሩ የድርጅታችንን ኢህአዴግን ስም ለማጥፋት የፈጠረው የሀሰት ውንጀላ ነው በማለት አስተባብለዋል።

ስለጉዳዩ በቅርበት የሚያውቁትን የ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ  የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሀላፊዎችን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት ግን፤ ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ ሊሳካ አለመቻሉን ነው ጋዜጣው የጠቆመው።

በቀጣዩ ሳምንት የማኅበሩ ሥራ አስፈፃሚ ተሰብስቦ ማኅበሩ እየገጠመው ባሉት ችግሮች እና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ አቋም ለመያዝ በዝግጅት ይገኛል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide