ግንቦት ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-” የኢህአዴግ አባላትን ፖለቲካዊና ርእዮተ-ዓለማዊ ብቃት ለማሳደግ ለአርሶ አደሩና ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት ላላቸው አባላት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣንና ከፍ ያለ የትምህርት ዝግጅት ላላቸው ደግሞ አዲስ ራእይ መጽሄትን እና አብዮታዊ ዲሞክራሲ መጽሄትን የይዘት እና የስርጭት ለውጥ በማድረግ ” ለማሰራጨት ቢሞከርም ፣ አመራሩም አባላቱም ለማንበብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለኪሳራ ተዳርገናል በማለት ድርጅቱ አስታውቋል።
ይህ የተገለጸው ብአዴን “የ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ግምገማዎች ፣ የተላለፉ ውሳኔዎችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ” በሚል ርእስ ለከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሩ ባዘጋጀው ሰነድ ላይ ነው። ይህ 43 ገጽ ያለው ወረቀት ብአዴንም ሆነ ኢህአዴግ ያገጠመውን ችግር በዝርዝር ያቀርባል።
የአመራር አመላመልን እና ድርጅቱን እየለቀቁ የሚሄዱ አባላት መብዛትን በተመለከተ የገጠመውን ፈተና ሲዘረዝር ” ድርጅታችን ገዢ ፓርቲ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሥራ ታታሪ ያልሆኑና በድርጅቱ ሥራ ለመቀጠር አልያም ስልጣናቸውን ተጠቅመው በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ኃይሎች እየተቀላቀሉ ህልማቸው አልሳካ ሲላቸው ለቀው የሚሄዱ አባላት ቁጥር ትንሽ አይደለም” ብሎአል።
“በገጠር ታታሪ አባላት ቢመለመሉም ራሳቸውን ማውጣት እንጂ ሌላውንም መርቶና ደግፎ ለማሳደግ በቂ ትኩረት የማይሰጡ አባላት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም” የሚለው ድርጅቱ፣ በከተሞች በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በሲቪል ሰርቪሱና በትምህርት ተቋማት ምሁራን ላይ የትኩረት መስኮች ብለን በለየናቸው በቂ አባላት ካለመመልመላቸውም የተነሳ፣ የተመለመሉትም ከሥራ ትጋት ማነስ፣ ከህዝባዊ ወገንተኝነትና ከዓላማ ጽናት ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚስተዋሉባቸው ሆነዋል ብሎአል።
የድርጅቱን ልሳናት በተመለከተ የገጠመውን ፈተና ሲያትት ” በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ የይዘትና የሥርጭት ለውጥ ለማምጣት የዝግጅት ለማሻሻል ጥረት የተደረገ ቢሆንም ልሳኑ ከአባላት አጥር ወጥቶ ሁሉም አርሶ አደር ዘንድ እንዲደርስ አልሞ አልተንቀሳቀሰም ” ብሎአል።
አዲስ ራዕይ መጽሔትን በተመለከተ ደግሞ ” በወቅታዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ በቂ ትንተና የሚቀርብበት መጽሔት ቢሆንም ለመጽሔቱ ትኩረት የማይሰጡ አባላት ቁጥር ትንሽ አይደለም። መጽሔቱን ከወሰዱም በኋላ ከማንበብና ከመወያየት ይልቅ፣ ሳያነቡና ሳይወያዩ የሚቀሩ አደረጃጀቶች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። መጽሔቱን አንብበው ከሚያገኙት እውቀት በላይ ለመጽሔቱ የሚያወጡት ገንዘብ በልጦ የሚታያቸው አባላት ቁጥር ትንሽ አይደለም። በአመራሩም በኩል ቢሆን መጽሔቱ አንድ ዋና የአባላት አቅም መገንቢያ መሳሪያ ነው ብሎ በእምነት መያዝ ላይ ጉድለቶች አሉ። ” ብሎአል።
አብዮታዊ ዴሞክራሲ መጽሔትን በተመለከተ ሲገልጽ ” መጽሔቱ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚታተም ቢሆንም ከአመራር ጀምሮ አባላቱም ጭምር ለዚህ መጽሔት የሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ ነው። ዋናው ችግር የአመራሩ ነው። መጽሔቱ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ጥራት ያለው ጽሑፍ ይዞ እንዲቀርብ አልተደረገም። አመራሩም በቂ ተሳትፎ የለውም። በሥርጭት ረገድም ቢሆን ስለመጽሔቱ ፋይዳ በቂ ቅስቀሳ ተደርጎ አባላትና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው እንዲገዙት አልተደረገም። በመሆኑም የአመራሩንና የአባሉን አቅም የሚገነባ መጽሔት መሆኑ ቀርቶ ታትሞ በአግባቡ ስለማይሠራጭ ኪሣራው ድርጅታችንን ተጨማሪ ወጭ የሚጠይቅ ሆኖ ይገኛል። ” ብሎአል።
” አመራሩና አባላት አደገኛ የሆነ የንድፈ-ሃሳብ ድህነት የሚታይባቸው በመሆኑ ይህን ከንባብ ባህል ዝቅተኝነት ጋር የተያያዘ የፖለቲካዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ ግንዛቤ ዝቅተኛነት በአሳሳቢነቱ ተመልክቶ ለማስተካከል ሁሉም በያለበት ርብርብ ሊያደርግ ይገባል” ብሎአል ።
ከድርጅቱ ሰነድ ለመረዳት እንደሚቻለው በክልሉ ውስጥ የሚታየው ድህነት፣ የመልካም አስተዳደር እና ማህረበራዊ ችግሮች መሰረታዊ ምክንያት የአመራር ድህነት ነው።