ኢህአደግ ጥራት ያለው አባል ማግኘት አልቻልኩም አለ

ነኅሴ ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በመቀሌ ከተማ ሰማእታት አዳራሽ ዛሬ ሲጀምር በጽሁፍ ባሰራጨው ሪፖርቱ የአባላት ጥራት ችግር እንደገጠመው ይፋ አደርጓል።
ሪፖርቱ እንደሚለው አባላት ስለድርጅቱ ታሪክ ፣ፕሮግራም፣እሴቶችና ህገደንብ ዝርዝር ግንዛቤ ሳይዙ የሚመለመሉበት ሁኔታ አለ። “በእኛና በተቃዋሚዎች መካከል ስላለው መሰረታዊ ልዩነት ፣ስለመድረኩ ባህሪና ፈተናዎቹ በቂ መነሻ እውቀት ይዘው የእጩነት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደሙሉ አባልነት እንዲሸጋገሩ ለማድረግ የሚሰራው ስራም ከጉድለት የተላቀቀ አይደለም። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ አባላትም ለጥቅም ማግኛ አማትረው ድርጅቱን የሚቀላቀሉ ናቸው” ሲል አማሮአል።
በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት ጥራት ያለው አባል መጥፋቱን የሚያወሳው ይህ ሪፖርት፣ በአሰላለፍ ረገድ የጎራ መደበላለቅ ማጋጠሙንም ጠቅሷል። በመንግስት ፖሊሲዎችና ልዩ ልዩ ሰነዶች ስልጠናዎች በተሰጠበት ወቅት፣ በመንግስት መ/ቤቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሉ አባላት የሚነሱ የተሳሳቱ አመለካከቶች አባል ካለሆነው ብዙም የተለዩ የማይሆኑበት ሁኔታ በስፋት መታየቱን ለአብነት አንስቷል።
የግንባሩ አባላት ጠባብነትና ትምክህተኝነትን እንዲሁም በሃይማኖት ሽፋን የሚከሰት አክራሪነትን በበቂ ሁኔታ ለመመከት የሚቸገር ፣አልፎ ተርፎም የእነዚህ አመለካከቶች ሰለባ ሆነዋል ሲል ይተነትናል።
ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የተጀመሩ ስራዎች መደናቀፋቸውን የሚያትተው ኢህአዴግ፣ “የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ስራዎች ያመጡት ለውጥ ቢኖርም ከጥራት ጉድለት ጋር ተያይዞ የሲቪል ሰርቪስ ተቁዋማት መሆን በሚገባቸው ደረጃ ላይ አለመድረሳቸው አባላችን ግንባር ቀደም ሆኖ ከሌላው ሰራተኛ በተለየ አኩሃን የተጫወተው ሚና ፣አለመኖሩን ያሳያል” በማለት የድርጅት አባላቱ ያላቸውን የጽናትና የብቃት ችግር አስቀምጦአል።
በጀማሪ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች ግንዛቤያቸው ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱንም ሪፖርቱ አመልክቶአል። ለመካከለኛና ጀማሪ አመራሩ ከተሰጡ ስልጠናዎች በተገኘ መረጃ መሰረት ጀማሪ አመራሩ በግንባሩ ፖሊሲዎች ላይ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ የሚያነሱዋቸው አንዳንድ ጉዳዮች ከኪራይ ሰብሳቢ ተቃዋሚ ሃይሎች አጀንዳዎች የማይለዩ ናቸው ሲል የገዛ አባላቱን ኮንኖአል።
ብአዴንን በ2007 ዓም ከተቀላቀሉ ከ200 ሺ አባላት መካካል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ድርጅቱን ለቀው መሄዳቸውን ብአዴን በሪፖርቱ አመልክቷል።
ሪፖርቱ ኢህአዴግ በየቀኑ የሚሰራው የፕሮፓጋንዳ ስራ በአባላቱ ጭምር ተቀባይነት እንዳላገኘ በተቃራኒው የተቃዋሚዎች አጀንዳ በኢህአዴግ አባላት ጭምር እየተደገፈ መምጣቱን የሚያመለክት ሆኗል። የገዛ አባሎቹ የድርጅቱን መርሆዎች ካልተቀበሉና ካላመኑባቸው፣ የሌላው ህዝብ ስሜት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም በማለት ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በርካታ የህወሃት ደጋፊ ወጣት አባላት ህወሃትን እየነቀፉ ነው። ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የትግራይ ወጣቶች አንዳንድ የህወሃት መሪዎችን እያነሱ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች እየተቹ ነው። ቀድሞ ህወሃት አይነካብን ይሉ የነበሩ ደጋፊዎች፣ በሰሞኑ ጉባኤ አቶ አርከበ እቁባይ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው እንዲመረጡ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ሰንብተዋል። ይሁን እንጅ አቶ አባይ ወልዱ ሊቀመንበር ሆነው መውጣታቸው እንደታወቀ፣ ወጣት ደጋፊዎች ” በትግራይ ተጨማሪ 5 የባርነት አመታት” በማለት ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ነው። ህወሃት ከ15 ዓመታት ወዲህ እንዲህ አይነት ጠንካራ ክፍፍልና ነቀፌታ በአባለቱ ዘንድ ሲያጋጥመው ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።