(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 27/2010)
ኡጋንዳ ለፕሬዝዳንትነት በሚወዳደሩ እጩዎች ላይ የጣለችውን የዕድሜ ገደብ አነሳች።
ርምጃው ፕሬዝዳንት ዮዎሬ ሞሶቬኒ እድሜያቸው ለተጨማሪ ፕሬዝዳንታዊ ውድድር አለመፍቀዱን ተከትሎ የተነሳ እንደሆነም ታውቋል።
የኡጋንዳ ፓርላማ በኡጋንዳ ሕገመንግስት ላይ የተቀመጠውን የዕድሜ ጣሪያ ያነሳው 317 ለ97 በሆነ የድምጽ ብልጫ እንደሆነም አልጀዚራ በዘገባው ላይ አስፍሯል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1995 የታወጀው የኡጋንዳ ሕገመንግስት ዕድሜው 35 አመት ያልደረሰና ከ75 አመት ያለፈው የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት እንዳይሆን ይከለክላል።
ሕገ መንግስቱ ሲወጣ የ50 አመት ጎልማሳ የነበሩትና ያኔም የሀገሪቱ መሪ የነበሩት ዮዎሬ ሞሶቬኒ ዛሬ ላይ የ73 አመት ዕድሜ ባለጸጋ ናቸው።
በሕገ መንግስቱ መሰረትም ከዚህ በኋላ ሞሶቬኒ በስልጣን ላይ መቆየት የሚችሉት ለሁለት አመታት ብቻ በመሆኑ ሕገ መንግስቱ ለፕሬዝዳንትነት እንዳይወዳደሩ ገድቧቸዋል።
በዚህ ሳቢያ በሕገ መንግስቱ የተቀመጠውን የዕድሜ ጣሪያ በማንሳት ለዳግም የምርጫ ውድድር ራሳቸውን ያዘጋጁት ሙሴቬኒ እቅዳቸው ተሳክቶ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ የዕድሜ ገደብ ጉዳይ በፓርላማው እንዲነሳ ተደርጓል።
ፓርላማው 317 ለ97 በመሆነ ድጋፍ ያሳለፈውን ውሳኔ በፊርማቸው ያጸደቁት ዮዎሬ ሞሶቬኒ ፓርላማውን አመስግነዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1986 በትጥቅ ትግል በመምራት መንግስታዊ ስልጣን የያዙት ዮዎሬ ሞሶቬኒ በመሪነት መንበር ላይ ከተቀመጡ 32 አመታት አስቆጥረዋል።