(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 30/2010) የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ እርቀ ሰላም ለማውረድ ተስማሙ።
ሁለቱ ወገኖች በሃገሪቱ ቴሌቪዥን በጋራ በሰጡት መግለጫ በቀጣይ ያሉ ልዩነቶችን በውውይት ለመፍታት መወሰናቸውን አስታውቀዋል።
በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ውጤቱን አልቀበልም በሚል የተፈጠረው ውዝግብ ለ150 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑን ነው ቢቢሲ በዘገባው ያስታወሰው።
ለረጅም አመታት በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ በተፎካካሪነት የቆዩት ራይላ ኦዲንጋ ፣ ኡሁሩ ኬንያታን ለሀገሪቱ አንዳች የፈየዱት ነገር የለም።–ይህ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ለምርጫ መወዳደራቸው ተገቢ አይደለም በማለት አስቀድመው ሲያውግዙ እንደነበር ይታወሳል።
ያንን ተከትሎም ውጤቱ ይፋ ሲሆን ራይላ ኦዲንጋ ውጤቱን አልቀበልም ከማለት አልፈው ራሳቸውን ፕሬዝዳትን አድርገው እስከ መሾም መድረሳቸውም ይታወቃል።
አሁን ላይ ታዲያ ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸውን በተወሰነ ደረጃ አጥበው እርቀ ሰላም ለማውረድ መስማማታቸው ታውቋል።
በኬንያ ከተካሄደው ምርጫና ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላ የመጀመሪያቸው ነው በተባለውና በሃገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት የጋራ መግለጫ ኡሁሩ ኬንያታና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ በቀጣይም በልዩነቶቻቸው ዙሪያ ቀጣይ ውይይቶችን ለማድረግ መወሰናቸውን አስታውቀዋል።
የዘር ሀረግን መሰረት ባደረገው የኬንያ ፖለቲካ በሁለቱም ወገኖች በኩል የሚደረጉ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች በሃገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋትን ያመጣል የሚል ስጋትን ያጭራል።
በግላቸውም ከደጋፊዎቻቸው ጋር በመሆን ራሳቸውን የህዝብ መሪ በማለት ቃለ መሀላ መፈጸማቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ ይህንን የበአለ ሲመት መርሃ ግብር የዘገቡ 3 የግል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተዘግተው እንደነበርም ሳይጠቅስ አላለፍም።
በዚህ ወቅት ሁለቱ ወገኖች ከዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት ምናልባትም የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴለርሰን በኬንያ የሚኖራቸውን ጉብኝት አስመልክቶ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተደረገ ሊሆን ይችላል ሲል ዘገባው አመልክቷል።