አፈናው ቢጨምርም ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ግን ተቃውሞአቸውን አጠናክረዋል

ሐምሌ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ረመዷን ፆም ከመግባቱ በፊት በአዲስ አበባ ትልቅ የ“ድምፃችን ይሰማ” የአንድነት ህዝባዊ ንቅናቄ ለማድረግና በፆም ወቅትም ለማስቀጠል በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ምንጮች አስታወቁ፡፡

በመጪው እሁድ ሐምሌ 8 ቀን 2004 ዓ.ም ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት እስከ አሥር ሰዓት ተኩል በአወሊያ መስኪድ ቅጥር ጊቢ በሚካሄደው ህዝባዊ አንድነትና የተቃውሞ ስብሰባ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ሙስሊም ማህበረሰቦችና ክርስቲያን ወንድምና እህቶች እንዲገኙ በክብር ተጋብዘዋል ሲሉ አንድ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ጊዜያዊ የኮሚቴ አባል ገልጸዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ላይ በግዳጅ የኢህአዴግ ካድሬ ስብስብ የሆነውን መጅሊስ እና የአህባሽን አስተምህሮ ለመጫን እየሞከሩነው ያሉን የኮሚቴ አባል የገጠሩ ማህበረሰብ በሃይማኖታችን መንግሥት ጣልቃ አይግባብን የሚለውን ተቃውሞ እንዳይቀላቀል መንገድ በመዝጋት፣ የመጓጓዣ መኪኖችን በማገት ሊያደናቅፍ ቢሞክርም ሰው በጋማ ከብትና በእግሩ እየተጓዘ በመሳተፍ ላይ ነው ብለዋል፡፡

እሁድ ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም ፒያሳ በሚገኘው በኒ (ኑር) መስኪድ በተካሄደው የአንድነት፣ የሰደቃ እና የድምፃችን ይሰማ ፕሮግራም ላይ የመንግስትና የአህባሽ ደጋፊ በመሆኑ በሙስሊሙ ማህበረሰብ የተገለለው የመጅሊስ የአመራር አባላት ስብሰባው ህገወጥ ነው ብሎ ለፌዴራል ፖሊስ በመጠቆሙ መስኪዱ በፖሊስ ተከቦ ነበር ሲሉ የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡

በእለቱ በኑር መስኪድ የሥነ-ሥርዓት አስከባሪ የሆኑ ኢማም ለዘጋቢያችን እንደተናገሩት ረፋዱ ላይ ጀምረው ዋናውን በር የተቆጣጠሩት ፖሊሶች ለህዝበ ሙስሊሙ ልናስገባ የነበረውን በርካታ ኩኪስ ብስኩትና የላስቲክ ውሃ አግተው ለራሳቸው የወሰዱት ሲሆን በሴቶች በር ያስገባነውን ቴምር ለተሰብሳቢው በማቃመስ የተቃውሞ ቆይታችንን አራዝመናል፡፡

ሁኔታው የደነቃቸው የእለቱ አሰጋጅም “ እነዚህ ሰዎች ምን ነካቸው እኛ ብስኩቱን ልንበላው እንጂ ልናፈነዳው አይደለም” በማለት ምሬታቸውን በምፀት ገልጸዋል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜናም ከሙስሊሞች ተቃውሞ እና ከዋልድባ ገዳም ጋር በተያያዘ በ ኢህአዴግ ውስጥ የጎላ ልዩነት እየተፈጠረ መምጣቱን ፍኖተ-ነፃነት ዘገበ።

ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ከስድስት ወራት በላይ ካስቆጠረው ሀገር

አቀፍ የሙስሊሞች ተቃውሞና በዋልድባ ገዳም ሊገነባ ከታሰበው  የስኳር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ በአባላቱ መካከል የጎላ ልዩነት መፈጠሩ ግንባሩን  አሣስቦታል።

ለግንባሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች  እንደጠቆሙት፤ ከሀይማኖት ጋር በተያያዘ በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ፤ ፓርቲው ከፍተኛ ባለስልጣናቱን በሀይማኖት ዙሪያ በተደጋጋሚ በማወያየት ላይ ይገኛል፡፡

በውይይቱም ሆነ በመወያያ ሰነዱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት የሰፈረው ነጥብ፤ <መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አለመግባቱን> ተሳታፊዎቹ በቀና ልቡና እንዲረዱ የሚያግባባና የሚማፀን  እንደሆነ አንድ ስማቸውን ያልገለፁ የስብሰባው ተሳታፊ ተናግረዋል

“ውይይቱ አስፈላጊ የሆነው፤ ከዝቅተኛ የፓርቲ አደረጃጀትና መዋቅር ጀምሮ ያሉ አባላት፦‹መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል› የሚል አቋም በመውሰዳቸው ነው፡፡” ብለዋል-እኚሁ ተሳታፊ።

ፓርቲው ፤ ውይይቱን በተለያዩ ደረጃዎች ማካሄዱን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

ኢህአዴግ፤ለዘመናት ተከብሮ የቆየውን የዋልድባ ቅዱስ ገዳም በዶዘር እያረሰ እንዲሁም ሙስሊሞች ፦”አህባሽ” የተሰኘ አስተምህሮ እንዲቀበሉና ባልመረጧቸው አመራሮች እንዲመሩ ጫና እያደረገ በሚገኝበት ወቅት፤ አባላቱን ሰብስቦ ፦”በሀይማኖት ጣልቃ አልገባሁም” ማለቱ፤ ዜናውን ያነበቡትን ሁሉ ያስገረመና ፈገግ ያሰኘ ሆኗል።

በስብሰባው አዳራሽ የኢህአዴግ አባላት ተነጣጥለው እንዲወያዩ ሲደረግ ፤ብዙዎቹ ተወያዮች በሙስሊሞች የወቅቱ ጥያቄና በዋልድባ ገዳም መደፈር ጉዳይ ላይ መንግስት እየተከተለ ያለውን አቋም አምርረው ሲተቹ እና ሲቃወሙ ተሰምተዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide