ኢሳት (ሰኔ 3 ፥ 2008)
ሰሞኑን በተለያዩ ክልሎች ተከስቶ የነበረው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ በአዲስ አበባ ከተማ መሰራጨት መጀመሩን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አርብ አስታወቀ።
በዚሁ በሽታ ምልክት የታየባቸው ሁለት ህሙማን በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ የተገኙ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ ወደ ጤና ተቋማት ገብተው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታው ስርጭት በአጭር ጊዜ ሊሰራጭ የሚችል በመሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ጥንቃቄን እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ይኸው ከመሰረታዊ የንጽህና መጓደል ጋር በተገኛኘ የሚከሰተው ተላላፊ በሽታ በተለይ ከውሃ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚከሰት መሆኑንና ታማሚዎች አፋጣኝ ህክምና ካላገኙ ለህይወት አስጊ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በከተማዋ ያለው የውሃ እጥረት በርካታ ሰዎች የዝናብ ውሃን ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲጠቀሙ በማድረጉ ሳቢያ በሽታው ሊቀሰቀስ መቻሉን ለመረዳት ተችሏል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የከተማዋ ነዋሪዎች ከበሽታው ስርጭት ራሳቸውን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርጉ ያሳሰበ ሲሆን፣ ነዋሪዎች ታማሚዎችን በአስቸኳይ ወደ ህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲወሰዱ አሳስቧል።
በቅርቡ በአርባ ምንጭ ከተማ ዙሪያዋ ባሉ መንደሮች ተቀስቅሶ የነበረው ይኸው በሽታ በርካታ ሰዎች ወደ ህክምና ጣቢያ እንዲገቡ ማድረጉ ይታወሳል።