ሚያዚያ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-“አገራችንን ለማዳን የቀረን ጊዜ ትንሽ፤ በጣም ትንሽ ነው። ስለዚህም በዚህ ወቅት ልቦቻችንና ክንዶቻችንን አስተባብረን በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ላይ እናንሳ” ሲል ግንቦት 7 ጥሪ አቀረበ
“አገራችንን ለማዳን እንፍጠን! ጊዜ የለንም” በሚል ርዕስ የንቅናቄው ልሳን ባሰፈረው ርዕሰ-አንቀጽ፤በደቡብ ኢትዮጵያ በቤንች ማጂ ዞን በጉራ ፋርዳ እና ሌሎች የዞኑ ወረዳዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተወላጆች በዓመታት ድካም ያፈሩትን ንብረት ተነጥቀው፤ ተደብደበውና ሰብዓዊ ክብራቸው ተደፍሮ በግፍ መባረራቸው ኢትዮጵያዊያንን ያስቆጣ ጉዳይ እንደሆነ ገልጿል።
“ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህ ዓለም ዓቀፍ ትኩረት የሚሻ ወንጀል ነው ብሎ ያምናል”ያለው ንቅናቄው፤” ይህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው። ይህ ወንጀል የተፈፀመው የመንግሥትን መዋቅር በተቆጣጠረ ወንበዴ መሆኑ አደጋው ጥልቅና ሰፊ እንዲሆን አድርጎታል”ብሏል።
“የሰሞኑ ክስተት የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ዘረኝነት እንደምን ያለ ከፍተኛና አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላካች ነው” ያለው ግንቦት 7፤ ከዚህ በላይ ምን እስክንሆን ወይም ምን እስከምንደረግ እንደምንጠብቅ መጠየቅ ያለብን ራሳችንን ነው”ሲልም እያንዳንዱ ዜጋ እየሆነ ስላለው ነገር ህሊናውን እንዲጠይቅ መክሯል።
“ለመሆኑ ዛሬም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ተጫጩኸን ዝም ነው የምንለው?፣ ዛሬም በየራሳችን ጎራ ላይ ቆመን አቅራርተን ነው የምንመለሰው?፣ዛሬም ራሳችንን እንደቁማር መጫወቻ ካርታ በመፐወዝ ጊዜና ጉልበት እናጠፋለን? ወይስ ይህን ግፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ተጨባጭ የሆነ የተግባር ሥራ ውስጥ በመሳተፍ በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ላይ ክንዶቻችንን እናነሳለን?”ሲልም ንቅናቄው ጠይቋል።
ግንቦት 7 አያይዞም፦”በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው በደል ዘልቆ የተሰማን መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን ስሜት ብቻውን በቂ አይደለም። ቁጭት ብቻውን በቂ አይደለም። ድርጊት ነው የሚያስፈልገው። ተግባር ነው የምንፈልገው። ወያኔን ድርጊት እንጂ ቁጭት አያስቆመውም”ብሏል።
ወያኔን ዛሬ በዚህ ካላስቆምነው ነገ ከዚህም የባሰ ነገር ውርደት ሊመጣ እንደሚችልም ንቅናቄው አስጠንቅቋል።
“በአገራችን ለዘመናት የቆየው የሕዝብ ለሕዝብ መከባበር ምን ያህል ይቆያል?፤ በዘርና በሃይማኖት ላይ የተመሠረተ ጠብን ሆን ብሎ የሚቆሰቁስ እኩይ ኃይል የመንግሥት ሥልጣን በተቆጣጠረበት አገር ውስጥ፤ የእርስ በእርስ መተላለቅ እንደማይመጣ ምን ማስተማመኛ አለን?”ሲልም በ አጽንኦት ጠይቋል- የንቅናቄው ርዕሰ አንቀጽ።
በግንቦት 7፣ የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የሁኔታዎች ትንተና መሠረት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በቋፍ ላይ ነች።
“እስካሁንም ያቆያት የሕዝቧ ቻይነትና አርቆ አስተዋይነት ነው”ያለው ንቅናቄው፤ “ በጥባጭ ቡድን የመንግሥትን ሥልጣን በያዘበት ሁኔታ መቻቻል ሁሌም ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም”ብሏል።
ንቅናቄው አያይዞም፦“የወያኔ ልማት በድሆች ላይ ላይ የመጣ ጥፋት ሆኗል። በዘር ላይ በተመሠረተ አድልዎ የተፈጠረው የሃብት ልዩነት እጅግ ሰፍቷል። ይህ ራሱ ወደ ከፋ የእርስ በርስ ግጭት ሊወስደን ይችላል። የግጭት ምክንያቶች በዝተዋል። ስለዚህም ጊዜ የለንም”ብሏል።
ርዕሰ-አንቀጹ በመጨረሻም፦”በግንቦት 7 እምነት አገራችንን ለማዳን የቀረን ጊዜ ትንሽ፤ በጣም ትንሽ ነው። ስለዚህም በዚህ ወቅት ልቦቻችንና ክንዶቻችንን አስተባብረን በመለስ ዜናዊ ፋሽስታዊ አገዛዝ ላይ እናንሳ’ሲል የትግል ጥሪ አቅርቧል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide