ሐምሌ ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢህአዴግ የወረዳ አመራሮች እንደሚሉት ባለፉት 26 ዓመታት አገሪቱ ባለቤት አልባ በመሆኗ ዝርፊያው ተጧጡፏል ። “ይችን አገር ከእንግዲህ ምን ልናደርጋት ነው?” ሲሉም ይጠይቃሉ።
አቶ መላኩ አምሳሉ ላለፉት 24 አመታት በተለያዩ የአመራር ቦታዎች ላይ ሰርተዋል። በእነዚህ አመታት ሁሉ የተረዱት ነገር ቢኖር አገሪቱ ባለቤት አልባ መሆኗን ነው። ሙስናው እና ቢሮክራሲው አለ፣ ነገር ግን እርምጃ የሚወስድ አካል የለም፤ ኢህአዴግ አይደለም አገሪቷን ማዳን ፣ ካዝናውም ማዳን አልቻለም፣ ካዝናው እየተዘረፈ ነው ይላሉ
አቶ ክብረት አበራ በበኩላቸው ፣ “እንደው ይችን አገር ምን ልናደርጋት ነው” ሲሉ ጠይቀው፣ ቀድሞ ኢህአዴግ መሬት መሸጥ መለወጥ በኢህአዴግ መቃብር ላይ ነው ይባል ነበር፣ አሁን መሬት የሚሸጠው ለጥቂት ባለሃብቶች ነው ይላሉ። አሁን ውሳኔ መስጠት የለም፣ ሁሉም ተፈራርቷል በማለት ውሳኔ ለመስጠት አስጋሪ መሆኑን ተናግረዋል።
በአገሪቱ ለሚታዩት ችሮችር ታች ያሉት የኢህአዴግ አመራሮች በላይ አመራሮች፣ እላይ ያሉት አመራሮች ደግሞ በታች አመራሮች በማሳበብ ከተጠያቂነት ነጻ ለመሆን እየሞከሩ ነው የሚሉት የድርጅቱ አባላት፣ በአጠቃላይ ድርጅቱ የራሱንም የአገሪቱንም ህልውና አደጋ ላይ ጥሏታል ይላሉ።