(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 25/2011)ህገመንግስቱና ፌደራሊዝሙ እንዲሻሻል አዴፖ መጠየቁን የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ገለጹ።
በፋኖ ስም በየመንገዱ መሳሪያ መያዝና ህገወጥ ስራ መስራት አይቻልም ሲሉም አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አምባቸው መኮንን ዛሬ ጎንደር ላይ በተዘጋጀ ህዝባዊ ስብስባ ላይ እንደገለጹት ህገመንግስቱንና ፌደራሊዝሙን ማሻሻልን በተመለከተ ቀድሞ ጥያቄ ያቀረበው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዴፓ ነው።
ዶክተር አምባቸው በፋኖ ስም የሚደረገው ህገወጥ ተግባርን በማውገዝ በዚህ ድርጊት ላይ የተሰማሩትን ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግስት ፀጥታ ጉዳዮችን ብቻ ነው እየሠራን መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዴፓ በህገመንግስቱና በፌደራሊዝም ዙሪያ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ መጠየቁን ነው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶር አምባቸው መኮንን የገለጹት።
በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ስብሰባ ነው።
በዛሬው ዕለት በተጠናቀቀው በዚሁ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አምባቸው ሕገመንግሥቱ እና ፌዴራሊዝሙ ጭምር እንዲሻሻል ቅድሚያ የጠየቀው አዴፓ ነዉ ብለዋል።
‹‹ይሄ የአዴፓ አቋሙ ነው፤ አሁንም አንቀፆችን በድጋሚ ከሕዝብ ጥቅም አንፃር ማየት እንደሚያስፈልግ እናምናለን፡፡ እኛ የአማራ እና የኢትዮጵያ መሪዎች ነን፤ የሁሉም ሕዝብ ጥቅም ጠንካራ ኢትዮጵያን ይፈጥራል ብለን ነው የምንሠራው›› ማለታቸው ተገልጿል።
ለኢሳት ከውስጥ ምንጭ በደረሰው መረጃ በቅርቡ በተካሄደው የኢህአዴግ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ይህው ጉዳይ መነሳቱ ታውቋል።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና በአብዛኛው የአዴፓ አመራሮች ድጋፍ ያለው የህገመንግስትና የፈደራሊዝም መሻሻል ሀሳብ በተወሰኑ የኦዴፓና በአብዛኛው የህወሃት አመራሮች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ነው የኢሳት የመረጃ ምንጮች የገለጹት።
የህወሀቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ የፌደራሊዝም ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው ለመጪዎቹ ሃምሳ ዓመታት ለውጥ አይደረግበትም ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ጎንደር ላይ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶክተር አምባቸው መኮንን አጽንኦት የተሰጠው ሌላው ጉዳይ በክልሉ ስጋት እየፈጠረ የመጣው ህገወጥነት ነው።
ከዚህ አንጻርም በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሃይሎች የሚፈጽሙትን ህገወጥ ተግባር እንዲያቆሙት ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል ።
ፋኖ አባቶቻችን ታሪክ የሠሩበት፣ ይህም ትውልድ ለሌላ ታሪክ የሚጠቀመው ስያሜ ነው፡፡
ነገር ግን በየመንገዱ በፋኖ ስም ሕገ ወጥ ሥራ መሥራትና የጦር መሣሪያ ይዞ መሄድ አይቻልም ነው ያሉት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶክተር አምባቸው መኮንን።
የክልሉ መንግስት ይህን ህገ-ወጥነት ሲያስታምም ቆይቷልም ሲሉ ተናግረዋል።
እነዚህን በፋኖ ስም ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙትን ሃይሎች የምትደግፉ ወገኖች ከድርጊታችሁ ተቆጠቡ ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አምባቸው ለወጣቱም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ራሳችሁን የማህበራዊ ሚዲያ አጀንዳዎች ማስተጋቢያ አታድርጉ ብለዋል ለወጣቶች ።
የጎንደሩ ህዝባዊ ስብሰባ በአማራና በቅማንት ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረውን ችግር በእርቅ በመፍታት ወሳኝ ውጤት ማስመዝገቡንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።