(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 22/2011) አዴፓ አቶ ደመቀ መኮንንና አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ።
የቀድሞው ብአዴን አዲሱ አዴፓ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌንና አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ 65 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መምረጡም ተመልክቷል።
ደኢሕዴንም ወይዘሮ ሙፍርያት ካሚልንና አቶ ሚሊዮን ማቲዮስን በድጋሚ መርጧል።
ደኢሕዴንም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑትን አቶ ፍጹም አረጋን ጨምሮ 65 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን መምረጡም ታውቋል።
የቀድሞው የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ የአሁኑ አዴፓ አቶ ደመቀ መኮንን እና አቶ ደጉ አንዳርጋቸውን ጨምሮ 13 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል።
ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ አቶ ብናልፍ አንዱአለም፣አቶ ተፈራ ደርበው እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለስራ አስፈጻሚነት ከተመረጡት ውስጥ ይገኙበታል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው ዶክተር ይናገር ደሴ፣አቶ ምግባሩ ከበደ፣አቶ ላቀ አያሌው፣አቶ ዮሃንስ ቧያለው፣አቶ ጸጋ አራጌ የአዴፓ ስራ አስፈጻሚ ሆነው መመረጣቸውም ተመልክቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢሕዴን/የፓርላማ አፈጉባኤ የሆኑትን ወይዘሮ ሙፍርያት ከማልንና የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ሚሊዮን ማቲዮስን ጨምሮ 15 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ዘይኑ ጀማል፣የቀድሞው የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ፣ከተመረጡት 15 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ውስጥ መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።
በኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹ ጉባኤ በርካታ ነባር አመራሮች በክብርና በመባረር የተሰናበቱ ሲሆን በአባል ድርጅቶቹ ጉባኤ የሁሉም ድርጅቶች ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመናብርት ባሉበት ቀጥለዋል።