አዲስ እየተቋቋመ ያለው ጠቅላይ አቃቤ-ህግ የፍትሃ-ብሄር ጉዳዮችንና አበይት የፍትህ ጉዳዮችን በበላይነት እንዲቆጣጠር መድረጉ የፍትህ ስርዓቱን ያጓትታል ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 27 ፥ 2008)

በቅርቡ ይፋ የተደረገውና በመቋቋም ላይ የሚገኘው ጠቅላይ አቃቤ ህግ የፍትሃ-ብሄር ጉዳዮችን ጨምሮ ሌሎች አበይት የፍትህ ጉዳዮችን በበላይነት እንዲቆጣጠር መድረጉ በፍትህ ስርዓቱ ክፍተት እንደሚፈጥ የተለያዩ አካላት ገለጡ።

ይኸው የፍትህ ሚኒስቴርን ህልውና እንዲያከትም የሚያደርገው ጠቅላይ አቃቤ ህግ የፌዴራል ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች የአቃቤ ህግ ተግባራትንም በበላይነት እንደሚቆጣጠረው በረቂቅ አዋጁ ላይ ተመልክቷል።

በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ላይ ስጋታቸውን የገለጹ የተለያዩ የሲቪክና የህግ ባለሙያዎች፣ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ የመመስረትና ክስን የማንሳት ተደራራቢ ሃላፊነቶች መያዙ አግባብ እንዳልሆነ መግለጻቸውን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

የጠቅላይ አቃቢ ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ ይፋ መደረግን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሁለት ሳምንት በፊት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሆነ መወሰኑም ይታወሳል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፍትሃብሄር ጉዳዮች እንዲሁም የአቃቤ ህግ ተግባራት በሚቋቋመው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ስር የሚጠቃለሉ ሲሆን ይኸው አዲስ የመንግስት አካልም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ታውቋል።

በዚሁ ረቂቅ አዋጅ አቃቤ ህግ ክስ ማንሳት ሲኖርበት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማማከር እንዳለበት የተቀመጠ ቢሆንም የህግ ባለሙያዎች አካሄዱ የፍትህ መጓተትን ያመጣል ሲሉ ቅሬታን አቅርበዋል።

በመንግስት ባለስልጣናትና ተቋማት ለበርካታ አመታት የሙስና ድርጊቶችን ሲያጋልጥ የቆየው የጸረ-ሙስና ኮሚሽን የተሰጠው ተልዕኮ ውስንነት ተደርጎበት በጠቅላይ አቃቢህግ ስር እንዲካተት መደረጉም ተቃውሞ እንዳስከተለ ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

ይኸው ውሳኔ የጸረ-ሙስና ትግሉን ወደኋላ የሚመልሰው እንደሆነ የህግ ባለሙያዎች ስጋታቸውን ቢገልጹም የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባየ የቀረበውን ቅሬታ አስተባብለዋል።

በመቋቋም ላይ ያለው ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የህግ ባለሙያዎች በበኩላቸው ሂደቱ በተለያዩ ነጻ የህግ ባለሙያዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች ዘንድ ሰፊ ውይይትን ማካሄድ እንዳለበት አክለው አሳስበዋል።