አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ከ5 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች አደጋ ላይ መሆናቸው ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 25 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ አዲስ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ መጋለጣቸውን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አረጋገጠ።

ለምግብ ድጋፍ ለተጋለጡ የሃገሪቱ ዜጎች በተያዘው አመት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በአደጋው በርካታ የቤት እንስሳት በመሞት ላይ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከወራት በፊት ባወጣው ሪፖርት በሃገሪቱ ተከስቶ ያለውን አዲስ የድርቅ አደጋ አፋጣኝ ርብርብ ካልተደረገለት ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚሁ አዲስ የድርቅ አደጋ ዙሪያ ማብራሪያን የሰጡ የመንግስት ባለስልጣን 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑ የሃገሪቱ ዜጎች ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ መጋለጣቸውን አስታውቀዋል።

ይህንኑ የድርቅ አደጋ ለመከላከልም 922 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በዚሁ አዲስ የድርቅ አደጋ በሶማሌ፣ ደቡብና፣ ኦሮሚያ ክልሎች ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ተመልክቷል።

ድርቁ ባስከተለው ችግርም አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህታቸውን አቋርጠዋል። ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች ተከስቶ በነበረው ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ 10.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ተጋልጠው እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና ባለፈው አመት የተከሰተው የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ሳያገኝ በሃገሪቱ አዲስ የድርቅ አደጋ መከሰቱ የእርዳታ አቅርቦቱ ስራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የዕርዳታ ተቋማት ይገልጻሉ።

መንግስት በበኩሉ ድርቁ የሚያደርሰውን ጉዳት ከወዲሁ ለመከላከል የዕርዳታ ድጋፍ ለማቅረብ ጥረት እየደተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

በተያያዘ ዜና የተባበሩት መንግስታት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በሃገሪቱ ተከስቶ ባለው አዲስ የድርቅ አደጋ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ አርብቶ አደሮች ለከፋ የውሃ እጥረትና የምግብ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል።

በዚሁ አዲስ የድርቅ አደጋ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚያስፈልገውን አጠቃላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ግብዓት ለማወቅ ጥናት በመካሄድ ላይ ሲሆን ውጤቱም በተያዘው ወር መገባደጃ ላይ ለህዝብ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል።

በቅርቡ ድርጅቱ በሰጠው ትንበያ ለዚሁ የድርቅ አደጋ መከላከል ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።

በሶማሊያ አፋርና የደቡብ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ እስከተያዘው የፈረንጆች አመት መጨረሻ ድረስ ዘላቂ ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል። ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ላይ ያሉ የጎረቤት ደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቁጥር በየዕለቱ በመጨመር በእርዳታ አቅርቦት ስራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩም ይነገራል።