አዲስአበባ ሌላ አወዛጋቢ ማስተር ፕላን ልታጸድቅ ነው

ጥር ፲፭ ( አሥራ አምስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስአበባ እና ፊንፊኔ ዙሪያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተግባራዊ እንደሚሆን ዝግጅት መኖሩን በመቃወም ሕዝባዊ ቁጣ ከተቀሰቀሰ በኋላ የተከለሰው የአዲስአበባ ማስተር ፕላን ላይ በየደረጃው ያሉ አካላት እየተወያዩበት ሲሆን የአዲስአበባ ከተማ ነዋሪዎችም ያሳተፉ ውይይት ለማካሄድ መታቀዱ ተሰምቷል፡፡
በአዲስአበባ እስካሁን ዘጠኝ ማስተር ፕላኖች ተዘጋጅተው ተግባራዊ የተደረጉ ሲሆን፣ የመጨረሻውና ዘጠነኛው ማስተር ፕላን የአገልገሎት ጊዜውን ያጠናቀቀው በ2005 ዓም ነበር፡፡ ይህን ለመተካት የተዘጋጀውና ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆን የነበረበት 10ኛው የተቀናጀ ማስተር ፕላን ከፍተኛ ተቃውሞ ካስተናገደ በኋላ የወረቀት ላይ ጌጥ ሆኖ እንዲቀር ተገዷል፡፡
የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን እቅዱ ደም መፋሰስ ካስከተለ በኋላ በይፋ መሰረዙ የተነገረ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ዓመት መጨረሻ ወደጎን ሳይሆን ወደላይ ማደግን ወይንም የረጃጅም ፎቆችን ልማት ታሳቢ ያደረገ አዲስ ማስተር ፕላን አውጥቶ በየደረጃው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን በማወያየት ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ከአዲስአበባ ከተማ ሕዝብ ጋር ውይይት ለማድረግ በአቶ ማቲዎስ አስፋው የሚመራው የአዲስአበባ ፕላን ኮምሽን እየተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡
አዲሱ ማስተር ፕላን ወደላይ ማደግን መሰረት ያደረገው በከተማዋ ያለው መሬት አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሐብቱን በጋራና በቁጠባ መጠቀም በማስፈለጉ ነው ተብሏል፡፡
አዲሱ ማስተር ፕላን በመሀል ከተማ በሚካሄደው የማስፋፊያ ስራ ምክንያት አሮጌ ፋብሪካዎች እየተነቀሉ ወደዳር የሚወጡ ሲሆን የከተማዋ በመቶ ሺ የሚቆጠር ነዋሪም በመልሶ ማልማት ስም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት እንደሚፈናቀል የፕላኑ ዕቅድ ፍንጭ ይሰጣል፡፡
በማስተር ፕላኑ መሠረት 10 የነበረው የክፍለከተሞች ብዛት ወደ 13 ከፍ እንደሚል የሚጠበቅ ሲሆን፣ የወረዳዎችም መጠሪያ ቁጥር መሆኑ ቀርቶ በስም እንዲሆን በፕላኑ ተካትቶአል፡፡ ማስተር ፕላኑ ከፒያሳ በቸርችል ጎዳና ወደብሔራዊ ቲያትርና ለገሀር ድረስ ያሉ አካባቢዎችን በዋና ማዕከልነት የያዘ ሲሆን የኢዮቤልዩ ቤተመንግስትና የመከላከያ ሚኒስቴር ወደሙዚየምነት እንደሚቀየሩ ይጠቁማል፡፡
ማስተር ፕላኑ በሚቆይበት 10 ዓመት ጊዜ ውስጥ በከተማዋ ስር የሰደደውን የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለመቅረፍ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ቤቶች ይገነባሉ የሚል ቢሆንም፣ የቤቶች ልማት ከጀመረበት 1996 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 13 ዓመታት በጠቅላላው የተገነቡት ቤቶች ቁጥር ከ180 ሺህ ያልዘለለ መሆኑ ሲታይ በብዙዎች ዘንድ ዕቅዱን ህልም አስመስሎታል፡፡