(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 26/2010) ሰማያዊ ፓርቲ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ህዝባዊ መንግስት እንዲቋቋም እንዲያደርጉ ጠየቀ።
ስድስት ጥያቄዎችን በማንሳት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ተግባር እንዲለውጧቸው ሰማያዊ ፓርቲ ጥሪ ያደረገው ዛሬ ባወጣው መግለጫው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ የተናገሩትን ወደ መሬት አውርደው በተግባር እስኪያሳዩን ስጋታችን ይቀጥላል ያለው ሰማያዊ ፓርቲ ስለኢትዮጵያ በክብርና በፍቅር ያደርጉትን ንግግር ግን በአድናቆት እንደሚመለከተው ጠቅሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቃላቸውን አክብረው ከህዝብ ለህዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲቋቋም በሚደረገው ጥረት ድልድይ ሆነው እንደሚሰሩም ተስፋ አለን ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ገልጿል።
ፓርቲው በመግለጫው የሰኞ ዕለቱን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ንግግር በአወንታዊ መልኩ እንደተቀበለው አስታውቋል።
ንግግራቸው ኢትዮጵያዊነትን በፍቅር ከማቀንቀን ጋር ተያይዞ ዘመን ተሻጋሪ ታሪኮችን በማጣቀስ ፣በፀና አንድነት ላይ መቆም እንደሚገባ ጥሪ ማስተላለፋቸው ከተለመደው ከኢህአዴግ ንግርት ውጪ መሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ በእጅጉ ያደንቃል ይላል መግለጫው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተቃዋሚ ሳይሆን ተፎካካሪ ናቸው ማለታቸውን የጠቀሰው ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠላት ሳይሆኑ ለዚህች አገር ሁለንተናዊነት አማራጭ ሀሳብ አንግበው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ፍትሃዊ የሆነ የመወዳደሪያ ሜዳው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሰፋ እንደሚገባ መናገራቸውን በበጎነቱ የሚታይ ብሎታል።
ይሁንንና ይህን በህዝብ ፊት የተናገሩትን ለመፈጽም የሚችሉ ስለመሆናቸው ጥርጣሬ እንዳለውም ሰማያዊ ፓርቲ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን ወደተግባር እንዲቀይሩት ያሳሰበው ሰማያዊ ፓርቲ ስድስት ጉዳዮችን በማንሳት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አድርጓል።
በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሲቪክ ማህበራትን በጠረጴዛ ዙሪያ በማቀራረብ የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ የሆነው ከሕዝብ ለሕዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲቋቋም በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን ሙሉ በሙሉ እንዲፈቱ፣ በህዝብ ላይ የተጫነውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያነሱ፣ በመላ አገሪቱ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሰው እንዲቋቋሙ ዜጎቻችንን ለዚህ ችግር የዳረጉ የመንግስት ሹመኞች በበደሉት መጠን ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲያደርጉ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በመግለጫው ጠይቋል።
የፍትህ ተቋማትና ምርጫ ቦርድን የመሳሰሉ ለመድበለ ፓርቲ መጠንከር እና ሊዴሞክራሲና ለፍትሕ እድገት ዋንኛ ማኖቆ በመሆን በገዢው ፓርቲ ጉልበት ሥር የተንበረከኩ በመሆናቸው እነዚህ ተቋማት በአዲስ መልክ ተዋቅረው በነፃነት ህዝብን እንዲያገለግሉ ማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠብቅ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ሰማያዊ ፓርቲ ገልጿል።
ነፃና ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን ከገዢው ፓርቲ መጠቀሚያነት ተላቀው ህዝብን በቅንነት እንዲያገለግሉ ማድረግ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሰው ፓርቲው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ ቁርጠኛ እርምጃ እንዲወስዱ በመግለጫው አሳስቧል።