አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ካለ ሕግ ማሰርን፣ በግዳጅ ማፈናቀልና ሰቆቃን ማስቆም አልቻሉም ሲል ሂውማን ራይትስ ሊግ ኦፍ ኢስት አፍሪካ አስታወቀ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 08 ቀን 2010 ዓ/ም) በቅርቡ በህወሃት ኢህአዴግ በሚመራው ወታደራዊ ኮማንድ ፖስት ወ/ሮ አያንቱ ሰኢድ የተባለች የድስት ወር ነፍሰጡር ሴት በምእራብ ሃረርጌ ዞን በቆቦ ከተማ መገደሏን ሂውማን ራይትስ ሊግ ኦፍ ኢስት አፍሪካ ይኮንናል። የአያንቱ እህት በቪኦኤ ሬዲዮ ላይ አፕሪል 10 ቀን 2018 በሰጠችው ቃለምልልስ እህቷ ራስዋን ልትከላከል ስትሞክር በሶስት ሊደፍሯት በመጡ ወታደሮች ተደፍራ መገደሏን ገልጻለች።
በተመሳሳይም አፕሪል 11 ቀን 2018 በምእራብ ኢትዮጵያ ቄለም ወለጋ ኮምቦ መንደር ነዋሪ የሆኑ የ70 ዓመት አዛውንት የሆኑት አቶ ማርዳሳ ያዴሳ በህወሃት ገዳይ ስኳድ አጋዚ ጦር በጭካኔ ተገለዋል። ልጃቸው ዲንቃ መርዳሳም ክፉኛ ቆስሏል።
ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ስልጣናቸው ከለቀቁበት ፌብርዋሪ 15 ቀን 2018 ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመከላከያ ሚንስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ አማካኝነት ከታወጀበት ከፌብርዋሪ 17 ቀን 2018 ጀምሮ ታጣቂዎች እኩልነትን፣ ነጻነትንና ፍትሕን የጠየቁ ሰላማዊ ዜጎችን ካለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የመግደል ልዩ መብት ተሰጥቷቸዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ ቁጥራቸው ከ63 ሽህ በላይ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ የሆኑ ቄሮ በመባል የሚጠሩ ወጣቶችን ጨምሮ የዞንና የወረዳ ባለስልጣናትና የፖሊስ ሰራዊት አባላት በአስቸኳይ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ወታደሮች አማካኝነት ካለሕግ እንዲታሰሩ ተደርገዋል።
በመላው ኦሮሚያ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆችና ዩንቨርሲቲዎች፣ የኮሚኒቲ ጽህፈት ቤቶች ያለው አፈና አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ከተመረጡ ወዲህ በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ተባብሰው ቀጥለዋል። በሃሮማያ፣ ጂማ፣ ወለጋና ሌሎች የኦሮሚያ ዩንቨርሲቲዎች በተማሪዎችና በታጣቂዎች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች ለወራት ተዘግተዋል። በ40 ዩንቨርሲቲዎች ውስጥ ወታደሮችን እንዲሰፍሩ በማድረግ ተማሪዎችን በመውረር እንዲታሰሩ ተደርገዋል። ታጣቂዎች ባደርሱባቸው ድብደባ የተጎዱ 36 ተማሪዎች በሃረር እና ድሬዳዋ ሆስፒታል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። የሶማሌ ልዩ ጦር አማካኝነት ኢሰብዓዊ በሆነ መልኩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች እንዲፈናቀሉ መደረጋቸውንና አሁንም ወደ ነባር ቀያቸው አለመለሳቸውንና ውጥረቱ አሁንም አለመርገቡን ሂውማን ራይትስ ሊግ ኦፍ ኢስት አፍሪካ አስታውቋል።