አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የኦህዴድን ፖለቲከኞች አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል

መስከረም ፳ (ኅያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ ክልል የሚገኙ የአዲስ አበባ አጎራባች ቀበሌዎችን ወደ ዋናዋ ከተማ የሚጠቀልለው አዲሱ ማስተር ፕላን ወይም ፍኖተ ካርታ፣ አርሶደሮችን ከመሬታቸው በማፈናቀል ለጥቂት የዘመኑ ባለሃብቶች ለመስጠት ተብሎ የተዘጋጀ ነው በማለት ተቃውሞ ያሰሙ የኦሮሞ ወጣቶች መገደላቸውንና መታሰራቸውን ተከትሎ፣ ለአንድ አመት ያክል ከመጽደቅ እንዲዘገይ የተደረው እቅድ እንደገና ለማጸደቅ የተጀመረው እንቅስቃሴ፣ የኢህዴድ አባላትን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል።
የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት አዘጋጅቶ ያቀረበውና የኦሮምያ የምክር ቤት አባላት እንዲሞሉት የሚያስገድደው ቅጽ፣ ፖለቲከኞችን አጣብቂኝ ውስጥ ጥሎአቸዋል። በቅጹ ላይ የምክር ቤት አባሉ ሙሉ ስም የሚጠየቅ ሲሆን፣ እያንዳንዱ አባል ከቀረቡለት ሶስት ጥያቄዎች መካከል አንደኛውን እንዲመርጥ ይጠየቃል። የመጀመሪያው አማራጭ ” ማስተር ፕላኑ ላይ የቀረበለትን ማብራሪያ በሙሉ ስለተገነዘብኩ እደግፋለሁ የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው አማራጭ ተጨማሪ ማብራሪያ እፈልጋለሁ፣ ሶስተኛው አማራጭ ደግሞ እቅዱ ስራ ላይ እንዳይውል እቃወማለሁ” የሚል ነው።
አብዛኛው የምክር ቤት አባላቱ እቅዱን የሚቃወሙት ቢሆንም፣ ስማቸውን አስፍረው ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ አልደፈሩም። ቅጹ እርስ በርስ እንዳይተማመኑና በአንድነት እንዳይቆሙ እንዳደረጋቸው አንድ የምክር ቤት አባላት ለኢሳት ገልጸዋል። አካሄዱ ማስተር ፕላኑን የሚቃወሙትን ለመለየትና ለመምታት ተብሎ መዘጋጀቱን የሚናገሩት አባላቱ፣ ከህዝብ ጋር ምክክር ሳይደረግ የሚተገበር እቅድ ደም አፋሳሽ ይሆናል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
ማምሻውን በደረሰን ዜና ደግሞ የምክር ቤት አባላቱ ተቃውሞ በማሰማታቸው፣ ውሳኔው እንዲዘገይ ተደርጓል።
ገዢው ፓርቲ እቅዱ በአዲስ አበባ ያለውን መሬት እጥረት በመቅረፍ ልማቱን ለማፋጠን ይረዳል በማለት መከራከሪያ ያቀርባል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አርሶአደሮች ባለፉት 24 አመታት ከመሬታቸው በብዛት ተፈናቅለዋል።