አውስኮድ እንደ ህብር ስኳር ሁሉ በሜቴክ መዘረፉን ሰራተኞች ተናገሩ

ጥር ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰራተኞች እንደገለጹት የአማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት /አውስኮድ/ከ2002 ዓ/ም ህዳር ወር ጀምሮ የጣና በለስን የተቀናጀ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ለመስራት ከፌዴራል መንግሥት የ6 ቢልየን ብር የግንባታ ስራ ውል ተሠጥቶት ሠራተኞች በሁለት ፈረቃ ቀንና ሌሊት በማሰራት የቦይ ሥራ ስርቶ አስረክቧል። የሸንኮራ አገዳው ዝግጁ እንዲሆን ቢደረግም፣ ፋብሪካውን እገነባለሁ ብሎ ኮንትራት የወሰደው በሜ/ር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው መከላከያ ኢንጂነሪንግ (ሜቴክ) ፋብሪካውን መስራት ተስኖት በ2006 ዓም በአቶ ሽፈራው ጃርሶ ትእዛዝ አውስኮድ ከሜቴክ እንደገና ኮንትራት (ሰብ ኮንትራት) ወስዶ፣ በፋብሪካው ቁጥር አንድ እና ሁለት ላይ ሰራተኞችን ከመደበኛ የስራ ሰአት ውጭ እንዲሁም በእረፍት ጊዚያቸው ሳይቀር እየሰሩ ፋብሪካው አሁን ላለበት ደረጃ አድርሰውታል።
ይሁን እንጅ ሜቴክ ምክንያቱን በግልጽ ሳያሳውቅ ለአውስኮድ መክፈል የነበረበትን 750 ሚሊዮን ብር ባለመክፈሉ ሰራተኞች ገንዘባቸውን በሜቴክ ተቀምተው ከበለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ መኖሪያ ካምፓቸውን ለቀው እንዲወጡ በመታዘዛቸው ወደ አውስኮድ ዋናው ካምፕ ጃዊ ወይም ፈንድቃ ከተማ እቃቸውን በማጓጓዝ ላይ ናቸው።
ሜቴክ ገንዘብ አለመክፈሉን ተከትሎ የአውስኮድ ከፍተኛ አመራሮች የድርጅቱን መዋቅር በአስቸኳይ ለመቀየር በሚል ምክንያት በዳንግላ ከተማ ከወር በላይ ለሆነ ጊዜ ተሰብስበው እየመከሩ ነው። ቀድም ብሎ ፋብሪካውን የመገጣጠም ሥራ ኮንትራት ወስዶ ስራውን ጀምሮ የነበረው የቻይና CWE በክፍያ ምክንያት በመስከረም 2009 ዓ/ም የተለያዩ መሳሪያዎቻቸውንና ተሽከርካሪዎቻቸውን ጭኖ ወጥቷል ፡፡
ሜቴክ የስኳር ፋብሪካዎችን እሰራለሁ በሚል የተለያዩ ኮንትራቶችን ቢይዝም አገሪቱን ለከፍተኛ ኪሰራ በመዳረጉ አብዛኛውን ፕሮጀክት እንዲቀማ ተደርጓል። ከውጭ በሚገኝ ብድር የሚገነቡት የስኳር ፕሮጀክቶች በተባለው ጊዜ ባለመገንባታቸውና አገሪቱም የብድሩን ወለድና አይነቱን የምትመልስበት ጊዜ በመድረሱ በአገሪቱ ባጀት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።