አውራ የኢህአዴግ ፓርቲዎች አዳጊ ክልሎችን ለማስተዳደር ስልጣን ተሰጣቸው

ጥር ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ እየተባለ የሚጠራውን ግንባር የመሰረቱት 4ቱ ፓርቲዎች ህወሃት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን አዳጊ ክልሎች እየተባሉ የሚጠሩትን ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሃረሪ፣ ድሬዳዋ፣ ሶማሊና አፋር ክልሎችን ለማስተዳደርና በበላይነት ለመምራት መከፋፈላቸውን ከኢህአዴግ ፅ/ቤት የተገኘው የውሰጥ መረጃ አመለከተ።

በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 52 ክልሎች ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣን የተሰጣቸው ሲሆን፣ ስልጣናቸውን ተጠቅመመውም የክልሉን የኢኮኖሚ፣ የመህበራዊና የልማት ፖሊሲ ስትራቴጂና እቅድ የማውጣት ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።

ይሁን እንጅ የፌደራሉ መንግስት እራሱ በሚወክላቸው አስፈጻሚዎችን አዳጊ የተባሉትን ክልሎች በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያስተዳደር ቢቆይም፣ አሁን ግን ግንባሩ አዳጊ ክልሎችን በመከፋፈል ለማስተዳደር ውሳኔ ላይ መድረሱን የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።

በዚህ አዲስ የስልጣን ድልድል መሰረት አዳጊ ክልሎች ያለ አውራ ፓርቲዎች እውቅና ምንም አይነት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን አያደርጉም።

አፋር ክልልን የሚያስተዳድረው አፍዴፓ በህወሃት ስር ሆኖ የአፋር ክልልን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ በክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ወቅትም የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው ይገኛሉ። በትግራይ ክልል የምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ግን የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት እና ምክትላቸው አይገኙም።

ኦሮምያን የሚያስተዳድረው ኦህዴድ በበኩሉ በህወሃት ደጋፊነት የሶማሊ ክልልን የማስተዳደር ሃላፊነት ሲሰጠው ፣ ሶማሊ ክልል በበኩሉ በኦህዴድ እየታገዘ ድሬዳዋን ያስተዳድራል።

የአማራውን ክልል የሚመራው ብአዴን በበኩሉ በአቶ ደመቀ መኮንን በሚሰጥ ውሳኔ የቤንሻንጉል ጉሙዝን እንደሚያስተዳድር ታውቋል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ግንኙነቱ ከብአዴን ጋር ይሆናል።

ኢህአዴግ የወሰደው ፖለቲካዊ እርምጃ በአዳጊ ክልሎች ውስጥ የሚፈጥረው የተለየ ስሜት እንደማይኖር የውስጥ ምንጮች ይገልጻሉ። ቀደም ብሎ አዳጊ ክልሎች በፌደራል ባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት ይተዳደሩ እንደነበር የሚጠቅሱት እነዚሁ ምንጮች፣ አሁን ዋናዎቹ ክልሎች አዳጊ ክልሎችን በመከፋፈል ለማስተዳደር በመወሰናቸው አዳጊ ክልሎች የሚያሰሙት ተቃውሞ አይኖርም ብለዋል።