ጥር ፲፰ ( አሥራ ስምንት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ በአቶ አብዲ ሙሃመድ የሚመራው የሶማሊ ክልል ልዩ ሚሊሺያ አባላት ወደ ኦሮምያ ድንበር በመግባት በርካታ ሰዎችን ከገደሉና ካፈናቀሉ በሁዋላ፣ የሁለቱ ክልል መሪዎች እርስ በርስ እስከመዘላለፍ የደረሱ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ የፌደራል መንግስት አዳማ ላይ አድርጎት በነበረው ስብሰባ ላይ የሁለቱም ክልሎች ሚሊሺያዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡና በስፍራው የመከላከየጣ ሰራዊት እንዲገባ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ይህንን ውሳኔ ወደ ተግባር ለመለወጥ ጥር 14 እና 15 በድሬዳዋ ከተማ የምዕራብና የምስራቅ ሃረርጌ የዞን ባለስልጣናት እንዲሁም የሁሉም የሶማሊ ክልል ዞኖች ባለስልጣናት በአቶ ካሳ ተክለብርሃን አማካኝነት ስብሰባ አድርገው የነበረ ሲሆን፣ በስብሰባው ላይ የሁለቱ ክልሎች የዞን አመራሮች የመከላከያ ሰራዊት በአስቸኳይ አካባቢውን እንደሚቆጣጠርና ትብብር እንዲያደርጉ ተነግሯቸዋል። በምስራቅና ምዕራብ ኦሮምያ የሚገኙ እንዲሁም የሶማሊ ክልል ሚሊሺያዎች በአካባቢው ከታዩ መከላከያ ሰራዊት እርምጃ እንደሚወስድባቸው ተገልጾላቸዋል።
በዚሁ ውዝግብ በበዛበት ስብሰባ አዲሱ የምስራቅ ሃረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መላኩ ፋንታ በድፍረት በሶማሊ ክልል አመራሮች ላይ ወቀሳ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሌሎች የዞኑ ባለስልጣናት ደግሞ የግጭቱ መንስኤ አቶ አባይ ጸሃየና ህወሃት ነው በማለት የጥቃቱ መንስኤ በደንብ እንዲመረመር ጠይቀዋል። “የሶማሊ ክልል ሚሊሺያዎች በራሳቸው እንዲህ አይነት ጥቃት ለመፈጸም ምንም አቅም የላቸውም፣ ጥቃቱ ኦህዴድን ሆን ብሎ ለማዳከም” በህወሃት በኩል የተደረገ ሴራ ነው በማለት አንዳንድ የኦህዴድ አመራሮች ሲናገሩ፣ በሶማሊ ክልል ባለስልጣናት ዘንድ ይህ ነው የሚል ምላሽ አልተሰጠም።
የሁለቱ አካባቢዎች ደንበር ለዘመታት ሲያወዛግብ ቆይቷል። አቶ አብዲ የሚመሩት ልዩ ሚሊሺያ በሶማሊ ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በተደጋጋሚ ሪፖርት አድርገዋል።
የሶማሊ ክልል ከአማራ ክልል ተፈናቀሉ ለተባሉ የትግራይ ተወላጆች የ10 ሚሊዮን ብር እርዳታ ከሰጠ በሁዋላ፣ ከወራት በሁዋላ የትግራይ ክልል በመልሱ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በሚል 12 ሚሊዮን ብር ለሶማሊ ክልል ለግሷል።