ህዳር 23 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አኬል ዳማ ተብሎ በመለስ መንግስት የተቀነባበረው የፈጠራ ድራማ ፣ የመለስ አገዛዝ ካልተገደደ በስተቀር በፈቃዱ ከዘረኛና አምባገነናዊ አቋሙ ፈቀቅ እንደማይል በማያሻማ ሁኔታ አሳይቶናል ሲል የግንቦት 7 ንቅናቄ ገለጠ ንቅናቄው “አኬልዳማን ይመልከቱ፣ መለስን ለማስወገድ ይነሱ” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ፣ አኬልዳማ ፊልም ” የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ምን ያህል ፈሪ እና በፍርሃቱም ምክንያት ምን ያህል ጨካኝ እንደሆነ ይረዳሉ። አገዛዙ እጁ ውስጥ የገቡ ሰዎችን ለማዋረድ የቱን ያህል ርቀት እንደሚሄድ ይታዘባሉ። ይህ የሥርዓቱ ባህርይ ገላጭ በመሆኑ ሁለገብ የትግል ስትራቴጂ ለምን እንደተመረጠ ይገነዘባሉ፤ እርስዎም ይቆርጣሉ። ይህንን ግፍ በዜጎቹ ላይ የሚፈጽም ሥርዓት ውሎ ማደር የሌለበት መሆኑን ይረዳሉ ብሎአል።
ግንቦት7 አክሎም በፊልሙ ” የመለስ ዜናዊ ዘረኛ ቡድን በግንቦት 7 የተግባር ሥራ ግራ መጋባቱ እና የሚይዘውና የሚጨብጠው የጠፋበት መሆኑን ይረዳሉ። ከጥቂት ጊዜዓት በፊት “ግንቦት 7 ወታደራዊ መዋቅሬን ቦርቡሮ መፍንቅለ-መንግሥት ሊያኪሂድብኝ ነበር” ብሎ ነበር። አሁን ደግሞ “ህጋዊ ተቃዋሚዎቼን ለዓላማው ማስፈፀሚያ አሰለፈብኝ” ይልዎታል። በዚሁ ፊልም “የግንቦት 7 አባላት እፍኝ አይሞሉም፤ አበነንኳቸው” ካለ በኋላ ወዲያው ደግሞ “ሴራቸው አላለቀም፤ የድርጅቴን መሪዎችና የአገዛዜን ባለሥልጣናት ሊገድሉብኝ ነው። ሕዝብ ሆይ! እንቅልፍ አጥተህ ዘብ ቁምልኝ” ሲል ያስደምሞታል። እንደ ጋዳፊም “ሕዝብ ይወደኛል፤ ይጠብቀኛልም” እያለ ያስቅዎታል። ሲል ይሳለቃል።
“እርሱ ራሱ በሻብያ ጀርባ ላይ ተንጠልጥሎ አራት ኪሎ እንዳልገባ ሁሉ “በሻብያ እየተረዱ ሊመጡብኝ ነው” ብሎ እሪ ብሎ ሲጮህ በመስማት ይዝናናሉ። እንዲሁም ሥልጣን ከመያዙ በፊት የሃገሪቱን ባንኮች፣ የጭነት መኪናዎችና አውቶቡሶች እየዘረፈ በሱዳንና በአረብ ሃገሮች የንግድ ሥራውን እንዳላጦፈ፤ ሥልጣን ከያዘም በኋላ ሌላው ሁሉ ቀርቶ የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ መሠረት 8. 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መስረቁን፤ ለም መሬታችን እየሸጠ መሆኑን፤ በብሄራዊ ባንክ ተቀምጦ የነበረውን ወርቅ በባሌስትራ ብረት ተክቶ መስረቁን ስለሚያውቁ “ግንቦት 7 ባንኮቼን ሊዘረፍ አስቧል” እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል እያዩ ይስቃሉ። ብሎአል ግንቦት7
ንቅናቄው አክሎም “ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት፤ ከወዳጅዎ ጋር ኢሜል መፃፃፍ፤ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ከጠራ ፓርቲ መሪ ጋር መነጋገር ከፍተኛ ወንጀል እንደፈጸመ ሰዉ በእድሜ ልክ ወይም በሞት የሚያስቀጡ መሆናቸውን ሲረዱ “እንዴት አድርጌ ልታገል” ለሚለው ጥያቄዎ ምላሽ ያገኛሉ። መብት እንዲከበርልዎ መለመንም ሆነ መጠየቅ እኩል የሚያስቀጡ ከሆነ የትኛውን መምረጥ እንዳለብዎ “አኬልዳማ” ግልጽ
በሆነ መንገድ ይነግርዎታል። ሲል የሰላማዊ ትግል መንገድ ችግር ውስጥ እየገባ መምጣቱን ተናግሯል።
በመጨረሻም በፊልሙ ውስጥ የወገኖቻችንን ስቃይ ሲመለከቱ መምህር የኔሰው ገብሬን ማስታወስዎ አይቀርም ያለው ግንቦት7 ፣ በፊልሙ መጨረሻ ላይ እንደተነገረው ሁሉ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ታጋዮች የመለስን ዜናዊን ዘረኛ አገዛዝ እያስጨነቁ መምጣታቸውንም ገልጧል።