አንድ ጄኔራል ኢትዮጵያ ውስጥ ታሰሩ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 1/2010)

አንድ የደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ጄኔራል ኢትዮጵያ ውስጥ መታሰራቸው ተሰማ።

ጄኔራሉ ለደቡብ ሱዳኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ታባን ዴንግ ጋይ የቅርብ ሰው ናቸው ሲል ራዲዮ ታማዙጅ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር የዋሉት ብርጋዴር ጄኔራል ጋች ቶች ባለፈው ጥቅምት ድንበር አቋርጠው በጋምቤላ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ሲዘዋወሩ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል።

ጄኔራሉ በቁጥጥር ስር የዋሉበት ምክንያት ምንም አይነት ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው ታርፓም በተባለ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ በኢትዮጵያ በመገኘታቸው ነው ተብሏል።

እናም የደቡብ ሱዳኑ ጄኔራል ላለፉት 3 ወራት በኢትዮጵያ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

ጄኔራሉ ወደ ኢትዮጵያ ያለፈቃድ የገባሁት ዘመድ ለመጠየቅ ነው ቢሉም የጋምቤላ ፖሊሶች ግን ሰውየውን ሕጋዊ ሰነድ የለህም በማለት በቁጥጥር ስር አውለዋቸዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግስት በጄኔራሉ መታሰር ጉዳይ ላይ እስካሁን የሰጠው መግለጫም ሆነ ምላሽ የለም።