ህዳር 19 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፖሊስ ሆስፒታል ምግብ አብሳይ የሆነችው ማርታ ጉልላት የተባለችው የ23 አመት ወጣት ፣ ህዳር 11 ቀን ሌሊት ላይ በሶስት የፌደራል ፖሊሶች ተደፍራ ህይወቱዋ አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ የደረሰን ዜና አመልክቷል።
የማርታ ጉልላት ቤተሰቦች ፖሊሶቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግስትን ቢጠይቁም፣ መንግስት ግን ጉዳዩን ሆን ብሎ እያጉዋተተው ለማወቅ ተችሎአል። የፌደራል ፖሊሶቹ ወጣቷ የተለመደ ምግብ የማቅረብ ስራዋን ስትሰራ በነበረበት ጊዜ በሀይል አስገድደደው ከደፈሩዋት በሁዋላ ጥለዋት ሄደዋል።
ወጣቱዋ ህክምና እየተከታተለች ቢሆንም አሁንም ደም እየፈሰሳት ና ህይወቱዋ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሎአል። የማርታ ቤተሰቦች አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ቢማጸኑም እስካሁን ድረስ መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም።
በዚች ደሀ ወጣት ላይ የደረሰውን ግፍ ለማጋለጥ የሴቶች ጉዳይ ተወካዮች ዝምታን መምረጣቸውንም የአካባቢው ሰዎች በሀዘን ይናገራሉ።
“እንደዜጋ በእኩል የማንታይበት አገር ላይ ነን” የሚሉት የወጣት ማርታ ጎረቤት፣ “በማርታ ላይ የደረሰው ግፍ ይህ ነው ባይባልም፣ ችግሩን የፈጸሙት የፌደራል ፖሊሶች በመሆናቸው ደፍሮ የሚጠይቃቸው
ጠፍቶአል” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጠዋል።