አንድ የእንግሊዝ ኩባንያ ከአፋር ክልል የፖታሽ ማዕድን ለማምረት ፈቃድ ተሰጠው

ኢሳት (መጋቢት 5 ፥2009)

መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገ አንድ የፖታሽ የማዕድን አምራች ኩባንያ በአፋር ክልል ለቀጣዮቹ 20 አመታት የማዕድን ሃብቱን ለማምረት የሚያስችለው ፈቃድ በኢትዮጵያ መንግስት እንደተሰጠው ማክሰኞ ይፋ አደረገ።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔን እንዲያገኝ ተደርጓል በተባለው በዚሁ ልዩ ፈቃድ ሲርከም (Circum) የተሰኘው ኩባንያ በብቸኝነት በአፋር ክልል በዳናክል አካባቢ ከአራት እስከ ዘጠኝ ቢሊዮን ቶን የሚጠጋ ፖታሽ ማዕድን ማምረት እንዲያችለው ማይኒንግ ዊክሊይ የተሰኘ መፅሄት ዘግቧል።

የማዕድን ኩባንያው በመነሻ ስምምነቱ ለ20 አመታት የሚቆይ ፈቃድ ቢሰጠውም የፕሮጄክቱ ዕድሜ በአስር አመት ሊታደስ የሚችል እንደሆነም ኩባንያው መገልጹን በማዕድን ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰራው መጽሄቱ አመልክቷል።

በአፋር ክልል የፖታሽ ማዕድን ስራውን ለመፈለግና ጥቅም ላይ ለማዋል በሚካሄድ ስራ የብሪታኒያው ኩባንያ ከሁለት እስከ ሶስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ካፒታል ወጪን እንደሚያደርግ ታውቋል። ኩባንያው አንድ ቶን የፖታሺየም ማዕድን ለማምረት የሚያወጣው 8 የአሜሪካ ዶላር በአለም ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱን ለመረዳት ተችሏል።

በተለያዩ ሃገራት በተመሳሳይ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ሲርከም ማዕድን ኩባንያ ከፍተኛ ጥራት ያለውና ለማዳበሪያነት የሚያገለግል ሁለት ሚሊዮን ቶን የሚገመት ምርትን በአመት ለማምረት እቅድ እንዳለው በድረ-ገጹ ካሰፈረው መረጃ ተመልክቷል።

ከአዲስ አበባ ከተማ በ600 ኪሎሜትር ርቀት በሰሜን ምስራቅ የአፋር ክልል የሚገኘው የዳናክል የፖታሺየም ፕሮጄክት በኢትዮጵያ በማዕድን ፕሮጄክቱ የሚታወቅና የበርካታ አለም አቀፍ የማዕድን ኩባንያዎችን ፍላጎት ስቦ መቆየቱን መጽሄቱ በዘገባው አስነብቧል።

ለ20 አመት የሚቆይ የማዕድን ማውጣት ስራ የተሰጠው የሰርከም የማዕድን ኩባንያ 365 ስኩዌር ኪሎሜትርን የሚሸፍን ሲሆን፣ ባለፈው አመት አንድ የእስራዔል ኩባንያ ከዳንክል ፕሮጄክት አዋሳኝ ላይ ተመሳሳይ ስምምነት ፈጽሞ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና የእስራዔሉ ድርጅት መንግስት የመሰረተ-ልማት ለማሟላት የገባውን ቃል አላከበረም በማለት ስምምነቱን በማቋረጥ ከኢትዮጵያ ጠቅልሎ ወጥቷል። በተመሳሳይ መልኩ ለበርካታ አመታት ለኢትዮጵያ የማዳበሪያ አቅርቦት በማቅረብ የሚታወቀው ያራ አለም አቀፍ ኩባንያ በአካባቢው የፖታሺየም ማዕድን ለማምረት ፈቃድ ማግኘቱም ታውቋል።

መቀመጫውን በኖርዌይ ያደረገው ይኸው ኩባንያ ለቀድሞ ሟች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሽልማት ማበርከቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ድርጅቱ ከሽልማቱ ማቅረብ በኋላ በኢትዮጵያ የማዕድን ስራ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ ማግኘቱን የማዕድን ድርጅቶች መረጃ ያመለክታል።

ይኸው ኩባንያ በአመት 600ሺ ቶን የማዕድን ማምረት ስራ ተግባራዊ ለማድረግ የፊሲቢሊቲ (feasibility) ጥእያካሄደ መሆኑን በድረ-ገጹ አስፍሯል።