ኢሳት (ግንቦት 22 ፥ 2009)
ንብረትነቱ የአንድ የአሜሪካ ወታደራዊ ኩባንያ የሆነ አውሮፕላን በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ከተማ በሚገኘው የኤዴን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ መከስከሱን ባለስልጣናት አስታወቁ።
መነሻውን ከዩንጋንዳ አድርጓል የተባለው ይኸው ወታደራዊ አውሮፕላን አራት የምዕራባውያን ሃገራት ዜጎችን አሳፍሮ የነበረ ሲሆን፣ በመንገደኞች ላይ ጉዳት አለመድረሱን የቻይናው ዜና አገልግሎት ሺንሁአ ማክሰኞ ዘግቧል።
ባንክሮፍት የሚባል ኩባንያ ንብረት የሆነው ወታደራዊ አውሮፕላኑ በአውሮፕላን ማረፊያው ለማረፍ በዝግጅት ላይ እንዳለ በሞተሩ ላይ የቴክኒክ ችግር አጋጥሞት የመከስከሱ አደጋ እንደደረሰበት ተመልክቷል።
የሶማሊያ አቪየሽን ሃላፌዎች አየር መንገዱ የደረሰበትን ችግር ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በአውሮፕላኑ ላይ የደረሰውን የመከስከስ አደጋ ተከትሎ የኤደን አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት መስጠት አቁሞ እንደነበር የዜና ወኪሉ በዘገባው አስነብቧል።
ባንክሮፍት የተሰኘው ኩባንያ በሶማሊያ ተሰማርቶ ለሚገኘው የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይል ወታደራዊ ስልጠናዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግም ለመረዳት ተችሏል። የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አልሸባብ በሃገሪቱ እያደረሰ ያለውን ጥቃት መጠናከርን ተከትሎ አሜሪካ በታጣቂ ሃይሉ ላይ አዲስ ወታደራዊ ዘመቻን እንደምታካሄድ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የተውጣጡ ወደ 21ሺ አካባቢ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በሶማሊያ ተሰማርተው ቢገኙም፣ የሚጠበቀውን ያህል ተልዕኮ እንዳልተወጡ ይገልጻል።
የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ከሃገሪቱ ለቆ መውጣት እንደሚጀምር በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል። ይሁንና የተለያዩ አካላት የሰላም ልዑኩ ለቆ ከመውጣቱ በፊት የሶማሊያ ጦር ሰራዊት አቅም መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።