ነሃሴ ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቀድሞ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፣ አሁን ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እየተባለ የሚጠራው ታዋቂው ድርጅት ባወጣው 127ኛ ልዩ መግለጫ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አርሲ ዞን በመንገድ ሥራ ላይ በተሰማራው የጃይናው CGCOC (ሲጂሲኦሲ) ዲራ ማኛ መቻራ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ማህበር የሆነው የዳንዲ ደራርቱ አርሲ ሰራተኛ ማህበር አመራርና አባላት በአሰሪዎቻቸው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየተፈጸመባቸው ነው ብሎአል። የሰብአዊ መብት ጥሰቱ ከተፈፀመ የቆየ ቢሆንም ለጉዳቱ ሰለባዎች ደህንነት ሲባል ይህ መግለጫ እንዲዘገይ መደረጉንም ሰመጉ ገልጿል።
ሰመጉ የዴራ ማኛ መቻራ መንገድ ሰራተኞችና የማህበሩ አመራር አባላት የተለያዩ የሰራተኛ መብቶች ይከበሩልን ብለው በመጠየቃቸው በCGCOC የቻይና መንገድ ስራ ተቋራጭ የተለያዩ አስተዳደራዊ በደሎች፣ እንግልት፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም የአስገድዶ መድፈርና የግድያ ሙከራ ጭምር እንደተደረገባቸውና አሁንም ህይወታቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ገልጿል።
በአቶ አረጋኽኝ ተፈሪ ላይ ከባድ ማሽን እላያቸው ላይ ተጥሎባቸው ከፍተኛ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ ጋሻው ጣሰው በተባሉት ላይ በማሰቃየትና የኬሚካል ርጭት በማድረግ በዘር ፍሬው ላይ ከባድ ጉዳት ማድረስ፣ በዳኜ ደጀኑ ቅኝ እጁንና እግሩን በስራ ላይ እያለ ቢያጣም ምንም አይነት ህክምና በአሰሪው በኩል ያልተደረገለት መሆኑን፣ ቱራ ሰማዲ በተባለው ላይ በሎደር ማሽን አፈር ተዝቆ እላዩ ላይ እንዲደፋበት መደረጉን፣ የማህበሩ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ኩራባቸው ፍቅሩ ዛቻ፣ ክትትልና የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው መሆኑ ተጠቅሷል። አቶ አውግቸው በቀለ ፣ አቶ ኤርምያስ ጥላየ እና አቶ ሀይሌ ጋዲሳ ደግሞ ዛቻና ክትትል እንዲሁም የመግደል ሙከራ ከተደረገባቸው በሁዋላ የደረሱበት አልታወቀም።
ወ/ሮ ገነት ወርቁ የተባሉ ሰራተኛም እንዲሁ ጾታዊ ጥቃትና አስገድዶ መድፈር ዛቻና ማስፈራሪያ ከተፈጸመባቸው በሁዋላ የደረሱበት አልታወቀም።
ቁጥራቸው 7 በሚሆኑ ሴት ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ላይ ቻይናውያን አሰሪዎቻቸው ፆታዊ ጥቃትና የአስገድዶ መድፈር ፈጽመውባቸዋል። ለሚመለከተው አካል ቢያመለክቱም «አርፈሽ ተቀመጭ» « ቻይናን መክሰስ አይቻልም» የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ለሰመጉ በምሬት ገልፀዋል፡፡
ሰመጉ ዝርዝር ወንጀሎችን በፎቶግራፍ ባመስደገፍ ያቀረበ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግስትና የክልል መንግሥታት ሰብአዊ መብቶችን በአግባቡ እንዲያስከብሩ እና ለመብቶችም የተጠናከረ ሕጋዊና ተቋማዊ ጥበቃ እንዲያደርጉም ጠይቋል።