ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2008)
ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ያስገኛል ተብሎ ከአምስት አመት በፊት ስራ የጀመረ አንድ ግዙፍ የቱርክ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ከመንግስት የተበደረውን ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈል ባለመቻሉ ለጨረታ ሊቅርብ መሆኑ ተገለጠ።
ፋብሩካው ያጋጠመው የፋይናንስ ችግር ወደ 1ሺ 200 ለሚጠጉ ሰራተኞች ስጋትን የፈጠረ ሲሆን፣ ኩባንያው ለውጭ ገበያ ሊያቅረብ ያሰበው ምርትም በከፍተኛ መጠን ቅናሽ ማስመዝገቡ ታውቋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ በምትገኘው ሰበታ ከተማ የሚገኘው ይኸው የጨርቃ-ጨርቅ ፋብሪካ ያጋጠመውን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ ከውጭ ሃገር አበዳሪ አካላት ጋር ድርድርን እያካሄደ እንደሚገኝ የኩባንያው የፋይናንስ አስተዳደር ሃላፊ የሆኑት ኦመር አሊ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በመንግስት ኩባንያ ወደ ሃገር ውስጥ ላስገባቸው ማሽነሪዎችና የተለያዩ ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነጻ እድልን ሲሰጥ መቆየቱ ታውቋል።
ይሁንና የቱርኩ ሳይጊን ዲማ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የተለያዩ ድጋፎች ሲደረግለት ቢቆይም የታሰበውን ውጤት ሊያመጣ አለመቻሉንና የፋብሪካው ህልውና አደጋ ውስጥ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
በሃገር ውስጥ ብድርን ለማግኘት የተደረገው ጥረት ውጤታማ ባለመሆኑ ምክንያት ፋብሪካው ደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ አበዳሪ ተቋማት ጋር ድርድርን እያካሄደ እንደሚገኝ የፋብሪካው የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ አክለው ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ያስገኛል ተብሎ ድጋፍ ሲደረግለት የቆየው ይኸው ፋብሪካ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረውን 625 ሚሊዮን ብር ሊከፍል ባለመቻሉ ባንኩ የፋብሪካውን ንብረቶች በጨረታ ለመሸጥ በዝግጅት ላይ መሆኑ በሃገር ውስጥ ያሉ የቢዝነስ ጋዜጦች ዘግበዋል።
በአመት ወደ 100 ሚልዮን ዶላር ገቢን ለማግኘት እቅድ የነበረው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በተያዘው በጀት አመት ወደ 40 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ብቻ ማግኘቱም ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በልዩ ድጋፍ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን ተከትሎ የመንግስት ባንኮች ለፋብሪካዎቹ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማበደራቸው ታውቋል።