መስከረም ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ስዊድንን በማስተዳደር ላይ ያለው የክርስቲያን ዲሞክራት ፓርቲ አባል የሆኑት ሚ/ር አንደርስ ኦስተንበርግ ስዊድን ለኢትዮጵያ በምትሰጠው እርዳታ እንዲሁም በአሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ እያደረገች ያለውን ጥረት በተመለከተ ለውጭ ልማትና እርዳታ ሚኒስትር ጥያቄ አቅርበዋል።
ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ነገር እንደሚያሳስባት ብትገልጽም፣ እኔ ግን አገሪቱ አስቸኳይ እርምጃ እንድትወስድ ጠይቄያለሁ ብለዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ በቅርብ እንደሚከታተሉ ለኢሳት የገለጹት ሚ/ር ኦስተርበርግ፣ የእርዳታ ሚኒስትሯ በቂ መረጃ አላቸው ብዬ አላምንም ብለዋል። አሁን ጉዳዩን ስላሳወቅን፣ የተሻለ ትኩረት ያገኛል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
በስዊድን ያሉ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በስቪክ ሶሳይቲ ድርጅቶች እንዲሁም በህዝቡ ውስጥ እየገቡ ስለኢትዮጵያ ማሰወቅ አለባቸው ያሉት የፓርላማ አባሉ፣ ምእራብ ሳሃራና ፍልስጤም በተደጋጋሚ በሰሩት የማሳወቅ ስራ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል። በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በተመሳሳይ በአገሪቱ የሚካሄደውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ማሳወቅ ይገባቸዋል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ገዢው ፓርቲ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን፣ የሲቪክ ሶሳይቲ መሪዎችንና ፖለቲከኞችን እንዲፈታ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ እንዲካሄድ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።