ኢሳት (ሚያዚያ 19 ፥ 2009)
መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገ የማዕድን ኩባንያ በኦሮሚያ ክልል ለወርቅ ፍለጋ በተሰጠው መሬት ላይ የሚኖሩ በርካታ ሰዎችን ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር የሚያስችል ዝግጅት መጀመሩን ይፋ አደረገ።
ከፊ ሚነራል የሚል መጠርያ ያለው ይኸው አለም አቀፍ ኩባንያ ከአንድ አመት በፊት ከመንግስት ጋር በደረሰው ስምምነት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ስር በምትገኘው የቱሉ ቃቢ አካባቢ የወርቅ ማውጫ ሰፊ ይዞታ ለ20 አመት መረከቡ ይታወሳል። ይኸው የወርቅ ማውጫ ፕሮጄክት በቀጣዮቹ ጥቂት ወራቶች ወደስራ እንደሚገባ ያስታወቀው ኩባንያው በይዞታው ላይ ያሉ በርካታ ሰዎችን ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የጋራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ለአክሲዮን ባለድርሻ አባላቱ ባሰራጨው መረጃ አመልክቷል።
የኩባንያው ሃላፊ የሆኑት ሃሪ አዳምስ ከቀያቸው የሚነሱ ሰዎች በቂ ካሳ የሚያገኙበትን ዝርዝር ዙሪያ ከመንግስት ሃላፌዎች ጋር ምክክር እየተካሄደበት እንደሆነ ገልጸዋል። ይሁንና የፌዴራሊምም ሆነ የክልሉ ባለስልጣናት ለዚሁ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ፕሮጄክት ምን ያህል ነዋሪ ከቀያቸው እንደሚፈናቀሉ የሰጡት መረጃ የለም።
የከፊ ሚኔራል ኩባንያ ከ500 በላይ የሆኑ የአካባቢው ሰዎችን አሰልጥኖ የስራ ዕድል ለመስጠት እቅድ መኖሩን ቢያሳወቅም ምን ያህል ነዋሪዎች ለረጅም ጊዜ ከኖሩበት መንደር እንደሚነሱ ዝርዝር መረጃን ሳይሰጥ ቀርቷል።
በኦሮሚያ ክልል ቱሉ ካፒ ያለው የወርቅ ክምችት 25 ቶን በላይ እንደሚሆን የማዕድን ሚኒስቴር ባለፈው አመት ካሰራጨው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
የወርቅ ክምችቱን ለማውጣት በዝግጅት ላይ የሚገኘው ኩባንያ በቀጣዮቹ 13 አመታት ከ 27ሺ ኪሎ ግራም በላይ ወርቅን ለማውጣት እቅድ እንዳለው አመልክቷል።
የአንድ ኪሎግራም ወርቅ በተያዘው ሳምንት 40ሺ ዶላር አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከፊ ሚነራል በኢትዮጵያ የተረከበው የወርቅ ማውጫ ፕሮጄክት ወደ ስራ ለመግባት ከጫፍ መድረሱን ባሳወቁ በሰዓታት ልዩነት የኩባንያ የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ በከፍተኛ ዋጋ የጨመረ ሲሆን፣ አዳዲስ ባለሃብቶችም በኢንቨስትመንቱ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ከኩባንያው ድረገጽ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ዋና መስሪያ ቤቱን በቆጵሮስ ያደረገው ይኸው ኩባንያ የፕሮጄክቱ መቶ በመቶ ባለቤት መሆኑም ታውቋል።
ከፊ ሚነራል የፕሮጄክቱ ስራ ለመጀመሪያ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከአክሲዮን ባለድርሻ አካባቢ ሲሰበሰብ የቆዩ ሲሆን በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የፕሮጄክቱን ስራ መጀመር አዘግይቶበት እንደነበር በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2013 አም መቀመጫውን በለንደን ያደረገና ኒዮታ የተሰኘ ኩባንያ የቱሉ ቆጲን የወርቅ ክምችት ቢያገኝም ፕሮጄክቱን ለማስጀመር ፋይናንስ ማሰባሰብ ባለመቻሉ ስራውን ለአሁኑ ኩባንያ ማስተላለፉን መረጃዎች ያመለክታሉ። የዚሁ የቱሉ ቆጲ የወርቅ ክምችት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1930ዎቹ በአንድ የታጣያን ኩባንያ ተገኝቶ መጠነኛ የወርቅ ማውጣት ስራ ይካሄድበት እንደነበረም ለመረዳት ተችሏል።