ነኅሴ ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሃምሌ 27 ቀን 2007 ዓም በደቡብ ክልል በጋሞጎፋ ዞን በጫኖ ሚሌ ቀበሌ ውብዬት ጩበሮ የተባለ የመከላከያ ሰራዊት አባል ፣ መከላከያን በመልቀቅ ወደ ቤተሰቦቹ ከተመለሰ ከሁለት ወር በሁዋላ፣ ፖሊሶች አንተ ተቃዋሚዎችን ትደግፋለህ ብለው በሰደፍ ደብድበው አንድ አይኑን እንዳፈሰሱት አባቱ አቶ ጩበሮ ጩኮ ለኢሳት ተናግረዋል።
ወታደሩ ወደ ቀየው ከተመለሰ በሁዋላ፣ ከአባቱ ጋር እርሻ ስራ እየሰራ ትምህርቱንም ለመቀጠል ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅት 5 ፖሊሶችና ታጣቂዎች በጋራ በመሄድ ክፍኛ ደብድበው እራሱን እስኪስት ድረስ ደብድበውታል። ወታደሩ ወደ ሆስፒታል በተወሰደበት ወቅት፣ ዶ/ር አንዱ አይን መጥፋቱን ማረጋጋጡንና ሁለተኛውን አይኑን ለማዳን ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውንና አሁንም ድረስ ህክምና እያደረጉለት መሆኑን አቶ ጩበሮ አስረድተዋል።
ፖሊስ ደርቅቴ ደራራ፣ ያልቄ የቴሌ፣ አለማየሁ አላሮ፣ ዘካሪያስ ፈንታና ሚሊሺያ ጳውሎስ የተባሉ ግለሰቦች ልጃቸውን መደብደባቸውን የሚናገሩት አባት፣ ጉዳዩን ለከፍተኛ ባለስልጣናት ለማመልከት እንዲሁም ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉም፣ መልስ የሚሰጣቸው አካል በመጥፋቱና በየቀኑ በሚደርስባቸው ዛቻ ምክንያት ለህይወታቸው በመስጋት አርባምንጭ ከተማ ዘመዶቻቸው ቤት ለማደር ተገደዋል።
ፖሊሶቹ ወደ ሆስፒታል እየሄዱ በሚፈጥሩት ጫና ከሃኪሞች ጋር መጋጨታቸውንም አቶ ጬበሮ ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳው ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።