ነኅሴ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከፍርድ ቤት ጋር በተያያዘ ለጊዜው ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቁ ምንጮች እንደገለጹት ፣ አንድ የህወሃት አባል 5 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ የሚገመት ጥሬ ገንዘብና ወርቅ በሻንጣው ይዞ ወደ ለንደን ሲገባ ጋትዊክ አየር ማረፊያ ላይ በፖሊሶች ተይዟል። ግለሰቡ ፍርድ ቤት ቀርቦአል።
ዳኛው ” ይህን ያክል ገንዘብ እንዴት በሻንጣ ልትይዝ ቻልክ የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ፣ ግለሰቡ ” ገንዘቡ የመንግስት መሆኑንና ለመንግስት ስራ ለማዋል መያዙን” ገልጻል። ይሁን እንጅ ዳኛው ” ይህን ያክል ገንዘብ በሻንጣህ የያዝከው በአገራችሁ ባንክ ስለሌለ ነው እንዴ? ” በማለት ጥያቄ አቅርበዋል።
ግለሰቡ በዋስ የተፈታ ሲሆን፣ መስከረም ላይ በድጋሜ ይቀርባል። ጉዳዩን በማስመልከት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስልክ ብንደውልም፣ መልስ የሚሰጠን አካል ለማግኘት አልቻልንም።
ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግርቲ በ8 አመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ 11 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ከአገር መውጣቱን ከሁለት አመታት በፊት ይፋ አድርጎ ነበር።