ኢሳት (የካቲት 28 ፥ 2008)
ከአዲስ አበባ ወደ ስዊድን ይጓዝ በነበረ አውሮፕላን ውስጥ በኮንቴይር ተደብቆ ውስጥ ተደብቆ ወደሃገሪቱ የገባ አንድ ኢትዮጵያዊ በስዊድን ጥገኝነት ጠየቀ።
ከ10 ሰዓት አስቸጋሪ በረራ በኋላ በስዊድን የደረሰ እና ማንነቱ እስካሁን ድረስ ይፋ ያልተደረገው ኢትዮጵያዊ በጥሩ ጤንነት ላይ መገኘቱን ስቶክሆልም ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ካሪና ካገርለንድ ኤክስፕረስ ለተሰኘ ጋዜጣ ገልጸዋል።
በሃገሪቱ የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቀው ኢትዮጵያዊ የተደበቀበት የእቃ ኮንቴይነር ግፊትን የሚቋቋም ቁስ የተገጠመለት በመሆኑ ህይወቱ ሊተርፍ መቻሉን ፖሊስ አስረድቷል።
በኦስትሪያ መዲና ቬይና ቆይታን አድርጎ ስዊድን መዲና ስቶክሆልም የደረሰው አውሮፕላን ጭነቱን ሊያራግፍ ባለ ጊዜ በአየር ማረፊያው ሰራተኞች ኢትዮጵያዊው ሊገኝ መቻሉን ጋዜጣው አስነብቧል።
ይሁንና፣ የስዊድን ፖሊስና የአርላንዳ አየር ማረፊያ በሃገሪቱ ጥገኝነት ስለጠየቀው የ28 አመቱ ኢትዮጵያዊ ማንነት ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ከስድስት ወር በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ሰራተኛ የነበረ የ24 አመት ወጣት በተመሳሳይ ሁኔታ ስዊድን ከገባ በሁላ ጥገኝነት መጠየቁ የሚታወስ ነው።
በአየር መንገዱ ወስጥ ያለን አድሎና ሃገሪቱ ያለውን አፈና በመቃወም አስቸጋሪውን ጉዞ ለማድረግ እንደተገደደ ወጣቱ ይርጋሸዋ ማሽላ በወቅቱ ለኢሳት በሰጠው ቃለ-ምልልስ ማስታወቁ ይታወሳል።
በአምባገነንነቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀም እንደምትታወቅና ባለፈው አመት በስዊድን ጥገኝነት ከጠየቁ ሰዎች መካከል አንድ በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ኤክስፕረስ ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
በሃገሪቱ የፖለቲካ ጥገኝነት ካቀረቡ ኢትዮጵያውያን መካከልም ግማሽ ያህሉ የመኖሪያ ፈቃድን እንደተሰጣቸው የስዊድኑ ጋዜጣ አክሎ አስነብቧል።
በጉዳዩ ዙሪያ የኢትይጵያ አየር መንገድ የሰጠው ምላሽ የለም።