አንድ ናይጀሪያዊ በቦሌ አየር ማረፊያ አደንዛዥ እፅ በሆዱ ውስጥ ደብቆ ለማለፍ ሲሞክር በቁጥጥር ስር ዋለ

ኢሳት (ታህሳስ 4 ፥ 2009)

በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አንድ ናይጀሪያዊ ከአንድ ኪሎግራም በላይ የሚመዝን ኮኬይን የተሰኘ አደንዛዥ እፅ በሆዱ ውስጥ ደብቆ ለማለፍ ሲሞክር በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ገለጸ።

በአየር ማረፊያው ሲደርስ የሆድ ህመም አጋጥሞት ነበር የተባለውና ስሙ ያልተገለጸው ናይጀሪያዊ ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል ተወስዶ አደንዛዥ እጽ በቀዶ ጥገና ከሆዱ መውጣቱን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ማክሰኞ ዘግበዋል።

84 የታሸገ ኮኬይን በሆዱ የተገኘበት መንገደኛ በሆስፒታሉ ከሶስት ሰዓት በላይ የፈጀ የቀዶ ጥገና ህክምና እንደተካሄደለት ታውቋል።

አደንዛዥ እፁን በሆዱ ደብቆ ለማለፍ ሙከራ ያደረገው መንገደኛ መነሻው ከብራዚል ሆኖ በቦሌ ኤርፖርት ትራንዚት ወደተለያዩ ሃገራት እንደሚሰራጭ ፖሊስ ገልጿል።

ከመንገደኛው አደንዛዥ እጹን የሚቀበል ቡድን በአዲስ አበባ መኖሩም ሊረጋገጥ እንደቻለ የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ቢሮ አመልክቷል።

ይሁንና ፖሊስ ከናይጀሪያዊው ጋር ግንኙነት አለው የተባለ ተጠርጣሪ ይኑር አይኑር የገለጸው ነገር የሌለ ሲሆን፣ አንድ ግራም ኮኬይን አደንዛዥ እፅ እስከ 200 ዶላር ድረስ እንደሚሰት መረጃን ያመለክታሉ።