አንድ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ተቃጠለ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 27/2010)

በሰሜን ጎንደር አንድ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ተቃጠለ።

በጭልጋ ወረዳ ነጋዴ ባህር አካባቢ ኳቤር ሎምዬ ቀበሌ ነዳጅ የጫነ ቦቴ መኪና ዛሬ ጠዋት የተቃጠለ ሲሆን፣  አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ለጥቃቱ ሃልፊነቱን ወስዷል።

ነዳጁ ለአጋዚ ጦር የታሰበ በመሆኑ ርምጃውን መውሰዱን ንቅናቄው አስታውቋል።

የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ነዳጅ የጫነ ቦቴ መቃጠሉን አረጋግጠው ቦቴው የጋየው ከዘራፊዎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ሊነጋ 11 ሰዓት ገደማ ነው። ነዳጅ የጫነ ተሳቢ ተሽከርካሪ ከሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ ኳቤር ሎምዬ ቀበሌ ደርሷል።

ይህ ቀበሌ የሚገኘው በሰሜን ጎንደር ጭልጋ ወረዳ ነጋዴ ባህር አካባቢ ነው። አርበኞች ግንቦት ሰባት እንዳስታወቀው የንቅናቄው ታጣቂዎች ለአጋዚ ጦር ነዳጅ በማጓጓዝ ላይ በነበረው ቦቲ ተሳቢ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ሙሉ በሙሉ እንዲወድም አድርገዋል።

ተሽከርካሪው ከጫነው ነዳጅ ጋር የተቃጠለ ሲሆን የንቅናቄው ታጣቂዎች ያቀዱትን ዘመቻ ከፈጸሙ በኋላ ወደቦታቸው መመለሳቸው ተገልጿል።

አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ርምጃውን ለመውሰድ የተገደደው  ነዳጁ በአካባቢው ህዝብ ላይ እየተንቀሳቀሰ ኢሰብአዊ ድርጊት ለሚፈጽመው የአጋዚ ልዩ ኮማንዶ ጦር ሊውል እንደነበር በማረጋገጤ ነው ብሏል።

በዚሁ በነጋዴ ባህር ኳቤር ሎሚዬ አካባቢ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ከጎንደር መተማ ወደ ሱዳን የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴያቸው የተገታ ሲሆን እስከምሽት ድረስ መንገድ ተዘግቶ እንደነበረ ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ተመሳሳይ ጥቃት ነዳጅ በጫነ ተሳቢ ተሽከርካሪ ላይ ሲፈጸም በ15 ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በነጋዴ ባህር መስመር ጎንደር ሲቃረብ አንድ ነዳጅ የጫነ ቦቴ መኪና መቃጠሉ ይታወሳል።

የዛሬውን ጥቃት በተመለከተ በግል ማህበራዊ ገጻቸው ላይ ምላሽ የሰጡት የአማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን በቅድሚያ የነዳጅ ቦቴ መቃጠሉን ካረጋገጡ በኋላ 5 ሰዓት ዘግይተው ስለ ቦቴው መቃጠል ማብራራያ ሰጥተዋል።

እንደ ሃላፊው አባባል ከሆነ የነዳጅ ቦቴው የተቃጠለው ከዘራፊዎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ነው።

በባለፈው ተመሳሳይ ጥቃት አቶ ንጉስ የተቃጠለው የነዳጅ ተሽከርካሪው አደጋው የደረሰበት በመገልበጡ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።

አርበኞች ግንቦት7 በገዢው ፓርቲ ወታደራዊ ተቋማት እና ንብረት ላይ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ሃላፊነቱን እየወሰደ ሲሆን፣ ርምጃውም በስልጣን ላይ ያለው የህወሃት አገዛዝ ጦር በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ስቃይ፣ አፈናና እንግልት ለመቀነስ ነው ብሏል።

በሰሜን ጎንደር የተሰማራው የአጋዚ ሰራዊት የትጥቅና የስንቅ አቅርቦት እንደልቡ እንዳያገኝ የሚያደርጉ ርምጃዎችን በመውሰድ በህዝብ ላይ የሚደረሰውን አፈና ለመቀነስ እንደታቀደም ከንቅናቄው የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

በሰሜን ጎንደር ከሱዳን በሚገቡ ነዳጅ የጫኑ ቦቲ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰውን ተደጋጋሚ ጥቃት ተከትሎ በአማራ ክልል በበርካታ ከተሞች የነዳጅ እጥረት የተከሰተ ሲሆን ረጃጅም ሰልፎች በየነዳጅ ማደያዎች መከሰቱን ለማወቅ ተችሏል።

ከወዲሁ ማደያዎች ዋጋ መጨመር የጀመሩ ሲሆን በብዛት ገዝተው የሚያጠራቅሙም እንዳሉ ተገልጿል።

የነዳጅ መኪና አሽከርካሪዎች ጥቃት ይደርስብናል በሚል ወደ ሱዳን ለመሄድ እንደማይፈልጉም ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።