አንድ በጥብቅና ሙያ ሲያገለግሉ የነበሩ ሰው ለተቃዋሚ አባል ጥብቅና በመቆማቸው እየተሳደዱ ነው

ግንቦት ፳፯(ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምስራቅ ጎጃም ዞን በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ሊበን ታየ የተባሉ አርሶ አደር የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆናቸው ብቻ በወረዳው ፖሊሶች ተደብድበውና ጭንቅላታቸው ላይ በሽጉጥ ተመትተው በሞትና በህይወት መካከል ወድቀው መገኘታቸውን ተከትሎ ፣ አርሶ አደሩ ከህመማቸው ሲያገግሙ ለወረዳው ጠበቃ ይገርማል መልካሙ አሰፋ ጉዳያቸውን ማመልከታቸውን ተከትሎ ችግሩ መጀመሩን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል። አቶ ሙጩ ዳኔ፣ አቶ ጓዴ መርሻና አቶ ሹመትና አቶ መራዊ መላኩ በተባሉ የወረዳው አመራሮች እንደተቀነባበረ በሚነገረው በዚህ ጥቃት አርሶ አደሩ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

ጠበቃ የገርማል አርሶ አደሩ ጉዳዩን ለወረዳው ፖሊስ እንዲያመለክት ምክር ቢሰጡም፣ አርሶ አደሩ እነሱ ድብድበውኝ እንዴት ክሴን ሊቀበሉ ይችላሉ በመለታቸው ከጠበቃው ጋር በመሆን በጋራ ሄደው በሚያመለክቱበት ጊዜ ፖሊሶች ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

አርሶ አደሩ የደም ሸማቸውን በመያዝ ጉዳዩን ለክልል ፖሊስ ኮሚሽን በማመልከታቸው፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽን አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ካደረጉ በሁዋላ ምርመራ መጀመሩን ለማወቅ ተችሎአል።  ድበደባውን ፈጽመውታል ከሚባሉት መካከል አቶ ጓዴ የተባለው ፖሊስ ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲገልጽ ሌሎች ፖሊሶች ግን ቃላቸውን ሰጥተዋል። የዚህ የምርመራ ውጤት ሳይገለጽ ከ6 ወራት በላይ ያለፈው ሲሆን፣ ጓዴ መርሻ የተባለው ፖሊስ ” የተቃዋሚ አባል እረድተሃል” በሚል በጠበቃው ላይ የግድያ እርምጃ እንደሚወስድ ሲዝት ቆይቷል።

የወረዳው ፖሊሶች ከካቢኔ አባላት ጋር በመመካከር የጠበቃውን የትዳር ጓደኛ በማስፈራራት ከትዳሯ እንድትለያይ ግፊት ማድረጋቸውን ተከትሎ ጠበቃው የትዳር ጓደኛቸውን ይዘው ወደ ዘመድ ሲሸሱ፣ ጓዴ መርሻ የተባለው ፖሊስ የመንግስት ታጣቂዎችን በመያዝ የጠበቃውን የትዳር ጓደኛ በሃይል በመውሰድ አግብቶ መቀመጡን ለማወቅ ተችሎአል።

ጠበቃው ጉዳዩን ለወረዳው ሚሊሺያ ሃላፊዎች እና ለመስተዳድሩ ባለስልጣናት ቢያመለክቱም ጉዳዩ የፖለቲካ ጉዳይ ስለሆነ ምንም ልንረዳህ አንችልም የሚል መልስ ተሰጥቷቸዋል።

ጠበቃ ይገርማልን አፈላልገን ለማግኘት የቻልን ሲሆን፣ ጠበቃው በእርሳቸው ላይ የተፈጸመው ድርጊት ሁሉ ትክክል መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው መቆየታቸው ለህይወታቸው አስጊ እየሆነ በመምጣቱ ጠበቃ ይገርማል ስራቸውን ትተው ራቅ ወዳለ ቦታ ተሰደው ከዘመድ ጋር መጠጋታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት መጠን ለመግለጽ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል። ለኢህአዴግ ህልውና አሳሳቢ ናቸው የሚባሉት ሁሉ በሃሰት ወንጀል እየተከሰሱ በደል እንደሚፈጸምባቸው ገልጸዋል።

ጠበቃው አርሶ አደሩን ለመርዳት የተነሳሱት ከሰብአዊ መብት አንጻር መሆኑን ተናግረዋል። ፖሊሱ ስልጣኑን መከታ በማድረግ የሰራው ስራ የአካባቢውን ህዝብ ማስቆጣቱም ታውቋል

በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።