አንድ ሱዳናዊ ሹፌር ኢትዮጵያዊቷን በጩቤ ወግቶ ከመኪና ላይ መወርወሩ ህዝባዊ ቁጣ አስነሳ

የካቲት ፳፬(ሃያአራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ድርጊቱ የተፈጸመው  ማክሰኞ የካቲት 24 ፣ 2007 ዓም ሲሆን አንድ የሱዳን ታርጋ ያለው ፣ በሱዳናዊ ሹፌር የሚሽከረከር ማዳበሪያ ያጫነ ከባድ መኪና  ከሱዳን ወደ ባህርዳር በመጓዝ ላይ ነው።

መኪናው እንፍራዝ እየተበላ በሚጠራ አነስተኛ ከተማ ላይ ሲደርስ አንዲት መኪና በመጠበቅ ላይ የነበረች ኢትዮጵያዊት ወጣት ሹፌሩን ትብብር ጠይቃው  ትሳፈራለች።  ምክንያቱ በውል ባይታወቅም፣ አንዳንዶች እንደሚሉት ሊደፍራት በመሞከሩና ፈቃደኛ ሆና ባለመገኘቷ ፣ ሹፌሩ ወጣቷን ደብድቦ፣  ሁለት አይኖቿን ካወጣቸው እና ወገቧን  በጩቤ ደጋግሞ ከወጋት በሁዋላ  ከወረታ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው   ቋህር  ቀበሌ ላይ ከመኪናው አውርዶ ወርውሯታል።

ድርጊቱ ሲፈጸም በሩቁ ያየ አንድ የሌላ መኪና አሽከርካሪ ቦታው  ደርሶ ወጧታ በሞትና በህይወት መካከል ስታጣጥር ያገኛታል። ወደ ወረታ በመጓዝ ላይ የነበረ ሌላ መኪና አስቁሞ ወጣቷን ወደ ህክምና ቦታ እንድትወሰድ ካደረገ በሁዋላ፣ ሹፌሩ ከባዱን መኪና ይከታተለዋል። ጉዳዩንም ለፖሊሶች ሪፖርት አድርጎ፣ ፖሊሶች ሹፌሩን ጉማራ ላይ እንዲያቆም ሲጠይቁት፣ ሹፌሩ ፈቃደኛ ሳይሆን ጥሶ ያልፋል።

ድርጊቱን በጭምጭምታ የሰሙት የሃሙሲት ከተማ ነዋሪዎች ድንጋይ ደርድረው የመኪናውን መምጣት ሲጠባበቁ ይቆያሉ። ሹፌሩ ተረጋግቶ ሃሙሲት ሲደርስ ነዋሪዎች አውርደው መደብደብ ይጀምራሉ። ፖሊሶች በመሃል ገብተው የሹፌሩን ህይወት ካተረፉ በሁዋላ፣ ወዲያውኑ የደህንነት ሃይሎች ሹፌሩን ወደ ወረታ ከተማ ወሰዱት።

የሹፌሩ መወሰድ ያበሳጫቸው ነዋሪዎች ፣ፖሊስ ጣቢያውን በመክበብ “በሰው አገር እየሞትንና እየተዋረድን ባለበት ሰአት በአገራችንም እንዲህ የምንሆን ከሆነ፣  ከባርነት የባሰ ኑሮ ነው የምንኖረው” በማለት ቁጣቸውን ሲገልጹ አርፍደዋል። ነዋሪዎች በሱዳንና በኢህአዴግ መንግስት መካከል ያለውን  ግንኙነት በመጥቀስ ሹፌሩ ይለቀቃል የሚል ስጋት እንዳላቸው ለኢሳት ገልጸዋል። የወጣቱዋን ወቅታዊ ሁኔታ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ይሁን እንጅ የአይን እማኞች የደረሰባት አካላዊ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ላትተርፍ ትችላለች በማለት ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ሱዳናዊው አሽከርካሪ ያለበትን ሁኔታ ለማጣራት ያደረግነው ሙከራም አልተሳካም።