ኀዳር ፲፪(አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንድነት ለዴሞክራሲያዊና ለፍትሕ ፓርቲ በመጪው 5ኛ ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ አስታውቋል፡፡
ፓርቲው በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማድረግ ሁኔታዎች ምቹ አለመሆናቸውን ቢጠቅስም “ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ ህዝቡ እንዲሳተፍ በመቀስቀስና በማበረታታት የተዘጋውን የዴሞክራሲ በር በምርጫ ካርዱ ሊያስከፍት እንደሚችል ከፍተኛ እምነት” እንዳለው አስታውቋል።
መንግስት የመድበለ ፓርቲን ስርዓት ለማጎልበት ምንም ዓይነት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከአሁኑ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመደርደር መሆኑን የገለጸው ፓርቲው፣ የአንድነት አመራሮችና አባላት በግፍ በማሰር ፓርቲው በምርጫው እንዳይሳተፍ ከፍተኛ የሆነ ጫና መደረጉን በዋቢነት አቅርቧል።
ኢህአዴግ ደጋፊዎቼ የሚላቸውን ብቻ በመራጭነት አስመዝግቦ ምርጫ የሚያደርግበት ሁኔታ እንዲያበቃ ደጋፊዎቻቸው በመራጭነት እንዲመዘገቡ ከማበረታት ጀምሮ የህዝብና የፓርቲ ታዛቢ በመሆን የምርጫ ሂደቱን በሙሉ በንቃት እንዲከታተሉ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።
“የኢትዮጵያ ህዝብ በገዥው ቡድን መልካም ፍቃድ ወይም በማንኛውም ውጫዊ ተፅዕኖ የፖለቲካ ምህዳሩን እንደማይሰፋ ሊገነዘብ ይገባል” የሚለው አንድነት፣ ምህዳሩ የሚሰፋውና ትክክለኛ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ የሚኖረው ህዝቡ በጠቅላላ ከፍርሀት ቆፈን ተላቆ በሙሉ ልብ ለመብቱ ሲቆም፣ ለፓርቲዎች ተገቢው
ድጋፍ ሲሰጥ፤ ከፍ ሲልም ወደ ትግሉ ሲቀላቀል ነው” በማለት በአገር ውስጥና በውጭ ላሉ ኢትዮጵያውያን መልእክት አስተላልፏል። ፓርቲው ከህዳር 14 እስከ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ መጀመሩንም ገልጿል።
በሌላ በኩል ሰማያዊ ፓርቲን ያቀፈው የ8 ፓርቲዎች የጋራ መድረግ በኢትዮጵያ ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ቅድመ ሁኔታዎች አልተማሉም በሚል የአንድ ወር የትግል መርሃ ግብር ነድፈው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ድርጅቶቹ ባለፈው እሁድ የጠሩት ስብሰባ በፖሊስ እንደተደናቀፈባቸው መዘገቡ ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ለነጻ ምርጫ የሚሆን ምቹ ሁኔታ የለም በሚል ምርጫውን እንደማይታዘብ እየገለጸ መሆኑን ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በአለም የምርጫ ታዛቢ በታአማኒነቱና በስራ ጥራቱ ቀዳሚ የሚባለው የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን፣ የምርጫ 97 እና 2002 ምርጫዎች
አለማቀፍ መስፈርትን እንደማያሟሉ መግለጹ ይታወሳል።