ሰኔ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆነው ወጣት ዳንኤል ተፈራ ለኢሳት እንደገለጸው ፓርቲው በሚቀጥሉት ሶስት ወራት እና ከዛም በሁዋላ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተሸራረፉ ያሉ ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ ይሰራል።
የጸረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ፣ የህዝብ ማፈናቀል እንዲቆም፣ የኑሮ ውድነቱ እና የስራ አጥነት ችግር እንዲቀረፍ፣ የንግዱ ማህበረሰብ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እንዲነግድ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እንደሚጠይቅ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።
ፓርቲው አላማውን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎችን በአዲስ አበባ እና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች እንደሚያደርግ፣ የአዳራሽ እና የአደባባይ ስብሰባዎችን እንደሚያዘጋጅ አስታውቀዋል
ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ማቀዱን አቶ ዳንኤል ገልጸው፣ ፓርቲያቸው መግለጫ ከመስጠቱ በፊት ከ 33 ፓርቲዎችን እና ከመድረክ ጋር መክሮ ቀጥሉ የሚል በጎ መላሽ አግኝቷል ብለዋል።