ሐምሌ ፲፩(አስራ አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፓርቲው በህገ ወጥ የዘመቻ እስር የሚሊዮኖች ድምፅ አይታጠፍም” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ የጸረ ሽብር አዋጁ በህገ መንግስቱ እውቅና የተቸራቸውን መብቶችን የሚጨፈልቅና ከህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ መሰረዝ ይገባዋል የሚሉ ዜጎች ወደ ዋናው የፓርቲው በጽ/ቤት በመምጣት የተቃውሞ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ የሚጠይቅ ‹‹ከሚሊዮኖች ለምን አንዱ አይሆኑም›› የሚል በራሪ ወረቀት በሁሉም የአዲስ አበባ ወረዳዎች ለማሰራጨት የተጀመረውን እንቅስቃሴ መታወቂያቸውን ለማሳየት በማይፈቅዱ ደህንነቶች ነን ባዮችና በፖሊስ ጥምረት በሕገወጥነት መንግድ እየተደናቀፈ መገኘቱ ” አሳዝኖኛል ብሎአል።
“ፖሊስ የአንድ ፓርቲ ወገንተኛ ሳይሆን ህዝብን ማገልገልና ሁሉንም በህግ መነጽር መመልከት የሚገባው አካል ቢሆንም ሚዛናዊነትን ባልጠበቀ ሁኔታ ህገ መንገስታዊ መብታችንን በመጠየቅ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የምናቀርበውን አቤቱታ ለማደናቀፍ መሞከሩና አባላቶቻችንን እግር በእግር እየተከታተለ ለእስር መዳረጉን በቸልታ ለመመልከት አንፈቅድም” አንፈቅድም ሲል ፓርቲው አክሎአል።
በራሪ ወረቀቶችን መበተን ከጀመርንበት ደቂቃ ጀምሮ አባሎቻችን እየታሰሩና ፍርድ ቤት እየቀረቡ ይገኛሉ ያለው አንድነት፣ ፖሊስ ፍርድ ቤት ባቀረባቸው ወጣቶች ላይም አንድነት የሚባል ፓርቲ መኖሩን አጣርቼ እስክመጣ የ10 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱና ፍርድ ቤቱም የተጠየቀውን መፍቀዱ የምንገኝበት ሰዓት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ እንድንገነዘብ አድርጎናል ብሎአል።
አንድነት በአባላቶቹና በእንቅስቃሴው ላይ የተከፈተውን ህገ ወጥ የፖሊስ ዘመቻ ለማስቆምና በደል ፈጻሚዎቹም በታሪክ፣ በህዝብና በህሊና ዳኝነት ይጠየቁ ዘንድ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያመራም አስታውቆ ፤ የጸረ ሽብር አዋጁ እንዲሰረዝ እያሰባሰበ በሚገኘው የህዝብ ድምጽ እንደሚገፋበትም ግልጽ አድርጎአል።