ጥር ፭(አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፍኖተ ነጻነት የፓርቲውን የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ አቶ ተክሌ በቀለን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታህሳስ 25 ቀን 2007 ኣመተ ምህረት ባደረገው ስብሰባ መጪውን ምርጫና ከምርጫው ጋር ተያይዘው ስለሚመጡ ጉዳዮች፤ እንዲሁም ከምርጫው በሁዋላ ፓርቲዎች ሊኖራቸው ስለሚገባው ትብብርና ውህደት የሚያመቻች ኮሚቴ ተቋቁሟል።
በስብሰባው፣ ፓርቲዎች በትብብርና በውህደት መስራት እንዳለባቸው ስራ አስፈጻሚው መምከሩን የተናገሩት አቶ ተክሌ ፤ ፓርቲያቸው ከመድረክ ጋር በትብብር ከሰማያዊና ከ መ ኢአድ ጋር ደግሞ ውህደት ፈጥሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ጫና በማሳደር አሁን ካሉበት ደረጃ ወደፊት መሄድ የሚችሉት ተባብረው አለያም ተዋህደው ሲሰሩ ብቻ ነው ብሎ ሚያምነው አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ፓርቲዎቹ እንዲዋሀዱ አለያም ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ እያደረገ ይገኛል።በተለይ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎቹ በምርጫ ቦርድ አማካይነት እያደረገባቸው ያለውን ከበድ ያለ ጫና ለመቋቋም ቢያንስ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ የሚመክሩ በርካታዎች ናቸው።
በሌላ በኩል ምርጫው በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት፡ከፓርቲዎች ጋር ውዝግብ ውስጥ ገባው ምርጫ ቦርድ አንድነትና መኢአድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ ውሳኔ ማሳለፉን እና ለሰማያዊ ፓርቲ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ማለቱን ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግባል።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ’፤የቦርዱን ስብሰባ ረግጦ ከመውጣትም በላይ ይቅርታ ለመጠ የቅ ፈቃደኛ አይደለም ላለው ሰማያዊ ፓርቲ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን የገለጸው ቦርዱ፤ ፓርቲው ማስጠንቀቂያውን የማያከብር ከሆነ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል ዝቷል።