አንዳርጋቸው ጽጌ ይፈታ በሚል ዘመቻ ተጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 29/2010) አንዳርጋቸውን ነፃ ማውጣት ኢትዮጵያዊነትን ማክበር ነው በሚል መሪ ቃል  ከዛሬ ጀምሮ እስከ ረቡዕ የሚቆይ  አንዳርጋቸው ፅጌ ይፈታ የሚል ዘመቻ በማህበራዊ ድረ ገፅ ተጀመረ።

በፌስ ቡክና ቲውተር የተጀመረው ዘመቻ የአንዳርጋቸውን ፎቶ ፕሮፋይል ስዕል በማድረግ፣ የእሱንና  የቤተሰቡን ፎቶግራፎች ከተለያዩ መልዕክቶች ጋር በማሰራጨት፣ስለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፖለቲካዊ ስብዕና የሚያጎሉ መጣጥፎችን በማጋራት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

ዘመቻውን በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን አክቲቪስቶች በጋራ የከፈቱት እንደሆነም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሰኔ 16 2006 ዓም ነበር አንዳርጋቸው በየመን አድርጎ ወደ ኤርትራ እያቀና የነበረው።

በየመን ርዕሰ መዲና ሰነዓ ላይ በየመን የጸጥታ ሀይሎች ታገተና ለህወሀት አገዛዝ ተላልፎ ተሰጠ። በህወሃት የማሰቃያ እስር ቤት አራት ዓመቱን ሊደፍን አንድ ወር ቀረው።

በእነዚህ አራት ዓመታት አንዳርጋቸውን ከአባቱ በቀር ሌላ ሰው እንዲጎበኘው አልተፈቀደም።

የህወሀት አገዛዝ አንዳርጋቸው ጽጌን እንዲለቅ በኢትዮጵያውያንና በአንዳንድ የእንግሊዝ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቢቀጥልም ተስፋ የሚሰጥ ውጤት ሊገኝ ግን አልቻለም።

ኢትዮጵያውያን በህወሃት አገዛዝ ላይ ያነሱትን መጠነ ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ቢፈቱም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በተመለከተ ምንም ነገር ሳይሰማ እስካሁን ቆይቷል።

በተለይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለህዝብ የገቧቸውን ቃሎች ተፈጻሚ እንዲያደርጉ የሚጠይቁት ኢትዮጵያውያን የአንዳርጋቸው ጽጌን መፈታት እንደአንድ ተስፋ ሰጪ ምልክት አድርገው ጫናቸውን ቢቀጥሉም የተለወጠ ነገር ሊታይ አልቻለም።

ይህ ሁኔታ ያስቆጣቸው በሀገር ቤትና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አክቲቪስቶች በአገዛዙ ላይ ጫና የሚፈጥርና ዓለም ዓቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያደርግ ዘመቻ ዛሬ በይፋ ጀምረዋል።

ለቀናት ቅሰቃሳ የተደረገበት ዘመቻ በማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ነጻ ወጥቶ ቤተሰቡን እንዲቀላቀል የሚጠይቅ እንደሆነም አዘጋጆቹ ይገልጻሉ።

ከዛሬ ሰኞ ሚያዚያ 29 እስከ ረቡዕ ግንቦት 1 2010 ወይም ከሜይ ሰባት እስከ ሜይ ዘጠኝ 2018 የሚደረገው የማህበራዊ ሚዲያዎች ዘመቻ አንዳርጋቸውን ነጻ ማውጣት ኢትዮጵያዊነትን ማክበር ነው በሚል መሪ ቃል እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል።

በዋናነት የሚተላለፈው መሪ መልዕክትም አንዳርጋቸው ጽጌ ይፈታ የሚል ነው።

ዘመቻውን የሚያስተባብሩት አክቲቪስቶች እንደሚገልጹት አንዳርጋቸውን ከእስር ቤት አስቀምጦ የሚደረግ የሰላም ንግግር ለውጥ አያመጣም።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እውነተኛ ማሻሻያ ማድረግ የሚችሉ መሆኑ ከሚፈተኑባቸው ርምጃዎች አንዱ አንዳርጋቸው ጽጌን ከእስር ነጻ ማድረግ ነው የሚሉት አስተባባሪዎቹ የዘመቻው ዓላማም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አመራር ላይ ጫና ለመፍጠር እንደሆነም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ በባህር ዳር  ሁለቱን የዋልድባ መነኮሳት ለመፍታት ብርቱ ፈተና እንደነበር መግለጻቸውን የሚጠቅሱት ታዛቢዎች የህወሃት መሪዎች አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ የተወሰኑ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዳይፈቱ ጠንካራ አቋም እንዳላቸው ይገልጻሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በህወሃቶች በተከበቡበት ሁኔታ አቶ አንዳርጋቸውን ለመፍታት የሚችሉ አይሆንም ይላሉ ታዛቢዎች።

በማህበራዊ ድረ ገጾች የአንዳርጋቸው ይፈታ ዘመቻ የጀመሩት አስተባባሪዎች በሶስት ቀናቱ እንቅስቃሴ አቶ አንዳርጋቸውን የሚገልጹ የፎቶ ግራፍ፣ የጽሁፍ፣ የድምጽና የምስል መልዕክቶችን በማሰራጨት ግፊት የማድረግ ዓላማ እንዳላቸው ይናገራሉ።

አቶ አንዳርጋቸው ከልጅነት እስከዕውቀት ያለፈባቸውን፣ የተጓዘባቸውን፣ ረጅም የትግል ህይወት የሚያንጸባርቁ የተለያዩ ጽሁፎችና ንግግሮች በሶስቱ ቀናት ዘመቻ እንደሚሰራጩም ገልጸዋል።

ዛሬ በተጀመረው በዚሁ ዘመቻ በፌስ ቡክና ቲውተር ላይ ያሉ የዘመቻው ተሳታፊዎች የገጻቸውን መለያ ፎቶ ግራፍ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምስል በመቀየር ዘመቻውን እያካሄዱት መሆኑ ታውቋል።