መጋቢት 17 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ትናንት እና ዛሬ በሶስተኛ ወንጀል ችሎት ጠባብ አዳራሽ በተካሄደው የመከላከያ ምስክሮችን የመስማት ሂደት ተከሳሾች በመከላከያ ምስክርነት ያቀረቡዋቸው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ዶ/ር ሀይሉ አርአያ እና አቶ ሙለቱ ጣሴ ቀርበው መመስከራቸው ታውቋል።
ችሎቱ በጠባብ አዳራሽ የተካሄደ በመሆኑ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ በመታደማቸውን ለማወቅ ተችሎአል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳን በስደተኝነት ከሚኖርበት አገር ታፍኖ ተወስዶ በእስር ላይ የሚገኘው አቶ አንዱአለም አያሌው ባለቤት ልጆቹዋን ለማሳደግ መቸገሩዋን ለኢሳት ገልጣለች።
ባለቤቱ እንዳለችው አቶ አንዱአለም አየለ በመጀመሪያ የተያዘው በሱዳን የደህንነት ሀይሎች ሲሆን ሱዳን ውስጥ ለአምስተ ቀን በእስር ላይ ከቆየ በሁዋላ በሶስት የደህንነት ሀይሎች ታጅቦ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ተወስዷል። የደህንነት ሀይሎች በድንበሩ ላይ እንደደረሱም በአንድ በረሃ ላይ ሲደርሱ አይኑን በጨርቅ ሸፍነው ከአንድ ግንድ ጋር አስረውት ለመግደል ሲዘጋጁ፣ አንደኛው የደህንነት አባል ይዛችሁ አስረክቡ ተባልን እንጅ ግደሉ ባለመባላችን በግድያው አልሳተፍም በማለቱ ህይወቱ ተርፏል። ሰራተኞቹም አንዱአለምን ብቻውን ባዶ በረሀ ላይ አስረውት ከሄዱ ከ2 ሰአት በሁዋላ ተመልሰው በመምጣት ለኢትዮጵያ የደህንነት ሀይሎች አስረክበውታል። ከዚያም በኢትዮጵያ የደህንነት ሀይሎች እጅግ አሰቃቂ ድብደባ ተፈጽሞበታል።
በአሁኑ ጊዜ የሁለት ልጆች እናት የሆነቸው ባለቤቱ ጥልፍ በመጥለፍ ልጆቹዋን ለማስተዳዳር ደፋ ቀና በማለት ላይ ብትሆንም፣ ኑሮዋን ለማሸነፍ እንደተሳናት ተናግራለች።
አቶ አንዱአለም አያሌው ለአምስት አመታት የፓርላማ አባል ሆኖ ማገልገሉ ይታወሳል።