ዜና (ሚያዚያ 5 ፥ 2008)
የወልቃይትን ማንነት በተመለከተ በተነሳው ጥያቄ ዙሪያ የአማራ ክልል ፕሬዚደንት፣ ከትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ጋር ፀብ ውስጥ መሆናቸው ተገለጠ። ይህንን የተናገሩት ራሳቸው የአማራ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሲሆኑ፣ የአማራ ምሁራን ከሩቅ ሆነው ከሚቃወሙ እንደ ትግራይ ተወላጆች ሃብት እንዲሰበስቡም ጥሪ ማቅረባቸው ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ በህክምና ላይ የሚገኙትን ባለቤታቸውን ለመጎብኘት በአሜሪካ የሚገኙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የወልቃይት ህዝብን የማንነት ጥያቄ በተመለከተ በርሳቸውና በድርጅታቸው በኩል የተያዘው አቋም የትግራይ ክልል መንግስትንና ህወሃት እንዳላስደሰተ ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ በርሳቸውና በትግራይ ፕሬዚደንት አቶ አባይ ወልዱ መካከል በግልፅ ጸብ መኖሩንም አመልክተዋል።
በዩኤስ አሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ራክቪል እና ቤተሳዳ በተባለው አካባቢ በሚገኘው ሰብኧርባን ሆስፒታል ባለቤታቸውን ለመጎበኘት የመጡት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከተለያዩ የአማራ ክልል ተወላጆች ጋር በግል መወያየታቸው የታወቀ ሲሆን፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡት አስተያየት እየተምታታ መገኘቱ፣ በሰላም በኩል እዚህ ከምትቃወሙ ሃገር ቤት ገብታችሁ እንደትግራዋይ ሃብት ሰብስቡ የሚል ጥሪ በማድረጋቸው ቅንነታቸውን የጠረጠሩ መኖራቸውም መረዳት ተችሏል።
እዚህ ሃገር የመንግስት ባለስልጣናት ሲመጡ የሚቃወሙ ሰዎች እንዳይደርሱብኝ በሚል አንድ የአሜሪካ ወታደር ከነበረ ኢትዮጵያዊ ጋር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም ለሚያገኙት ሁሉ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
ሃብት ይዘው ሃገር ቤት የገቢ ሃብታቸውን እጥተው እየተሰደዱና እየታሰሩ ባለበት እንዲሁም የፖለቲካ ስልጣንኑ በህወሃት ቁጥጥር ስር በቀጠለበት ሃገር ቤት ገብታችሁ ሃብት ሰብስቡ የሚለው ጥሪ የተቀነባበረ ዲያስፖራውን የመቅረብ ዘመቻ ሳይሆን እንዳልቀረ ተመልክቷል። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባለቤታቸውን ከመጠየቅ ጎን ለጎን ድርጅታዊ ስራ ደርበው መምጣታቸውም ተሰምቷል።
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቅርቡ ለተመሳሳይ ተልዕኮ በተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ዱባይ ቆታ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል።
አጎ ገዱ አንዳርጋቸው በወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ላይ ከትግራይ ክልላዊ መንግስት የተለይ አቋም ይዣለሁ፣ ከአባይ ወልዱ ጋርም ተጣልቻለሁ ቢሉም፣ የወልቃይት መብት ተሟጋቾች ሲታሰሩ እንዲሁም ጥያቄያቸው ከፌዴሬሽን ም/ቤት ሲመለስና የትግራይ ክልልም አልቀበልም ሲል ርሳቸውና የክልሉ መንግስት እንዲሁም ብዓዴን ከዝምታ በቀር የወሰዱት ዕርምጃ የለም።