መጋቢት ፮ (ስድስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 5ኛ ስብሰባ ከመጋቢት 4/2009 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ሃሙስ በሚደረገው ስብሰባ ጉባዔው አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ከስልጣን በማንሳት፣ አማራን በመዝለፍና በማዋረድ የሚታወቁትን አቶ አለምነው መኮንንን ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አንዳንድ የካቢኔ አባላት ህዝቡን ለማረጋጋት አቶ ገዱ ለ3 ወራት ያክል በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ሃሳብ ያቀረቡ ቢሆንም፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ፣ ሃሳባቸው ተቀባይነት አላገኘም። አንዳንድ የካቢኔ አባላት አቶ ገዱ ከስልጣን ከወረዱ ምናልባትም አመጽ ባልተነሳባቸው የክልሉ አከባቢዎች አመጽ ሊነሳ ይችላል የሚል አስተያየታቸውን ሲሰነዝሩ መሰማታቸውን ስብሰባውን የተከታተሉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
አቶ ገዱ ህዝቡ የጦር መሳሪያ እንዲታጠቅ ፈቅደዋል የሚሉና በክልሉ ያለውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ መቆጣጠር አልቻሉም የሚል ትችት ተሰንዝሮባቸዋል።
የኢህአዴግ ምክር ቤት የአቶ ገዱ ባላንጣ የሆኑትን የትግራዩን ገዢ አቶ አባይ ወልዱንም ከስልጣን እንዲነሱ ውሳኔ አሳልፎ የነበረ ቢሆንም፣ ህወሃት ከመጪው 3 ወራት በፊት አቶ አባይን ከስልጣን ለማውረድ ይቸግረኛል የሚል መልስ በመስጠት የኢህአዴግን ውሳኔ መሻሩ ታውቋል።
በአቶ ገዱ ደጋፊዎች በኩል የሚመጣውን ተቃውሞ ለመቀነስ በሚል አቶ ገዱን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አድርጎ ለመሾም የታቀደ ሲሆን፣ አቶ ገዱም ስለ አዲሱ ሹመታቸው ደብዳቤ እንደደረሳቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
አቶ ገዱን ለማውረድ የተጀመረው እንቅስቃሴ የቆየ ነው። ከአራት ወራት በፊት የህወሃት አባላት ብቻ በተሳተፉበት ስብሰባ አቶ ገዱ እንዲወርዱ አንዳንድ የህወሃት አባላት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ “አቶ ገዱን አሁን ማውረድ በክልሉ የሚታየው ተቃውሞ ተባብሶ እንዲቀጥል ማድረግ ነው፣ ሁኔታው ከተረጋጋ በሁዋላ፣ ከስልጣን እንዲወርዱ ይደረጋል” የሚል መልስ ተሰጥቷቸው ነበር። አቶ ገዱን የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ ለማድረግ የታሰበው በሂደት ከስልጣን በማስወገድ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል።
አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን የሚተኩት የአማራ ክልልን በመዝለፍ የሚታወቁት አቶ አለምነው መኮንን ሲሆኑ፣ በቅርቡ ከህወሃቱ ወይን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ለህወሃት በይፋ ይቅርታ አቅርበዋል።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረ እንዲሁም የአዊ ዞን የቀድሞ አስተዳዳሪና በኋላም የአማራ ክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ባዘዘው ጫኔም ከስልጣን እንዲነሱ ተደርጓል።