አቶ ዱባለ ገበየሁና ሁለቱ ዐቃብያነ ህጎች ክስ ተመሰረተባቸው

ጥር ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በዳውሮ ዞን ተነስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ አቶ ዱባለ ገበየሁ ፣   አቶ ጎሳሁን ዶሳ ዶሻና አቶ ግዛቸው ታደሰ ከበደ     ትናንት  ከሰዓት በኋላ ክስ ተመስርቶባቸዋል። ግለሰቦቹ  ሕዝብን በመንግሥት ላይ በማነሳሳትና በማሳመጽ ፣ ሕገመንግስ  ቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር  እንዲሁም የመንግሥትን ንብረት በአመጽ በማስወደም ወንጀል ተከሰዋል።

ኢሳት ያለውን የመረጃ ሰንሰለት ተጠቅሞ አቶ ዱባለን በእስር ቤት ውስጥ አነጋግሮታል::

ከዳውሮ ዞን ፖለቲካ ክፍል በተገኘው ምስጢራዊ መረጃ መሠረት በታሰሩት በእነ አቶ ዱባለ ገበየሁና በሌሎችም ላይ የሐሰት ማስረጃ ለማዘጋጀት እየተሰራ ነው።  ገንዘብ እየተከፈላቸው ለመመስከር የተዘጋጁ ሰዎች መኖራቸውን  ለማወቅ ተችሎአል።

በዞኑ የሚታየው አለመረጋጋት ያሳሰበው መንግስት ግለሰቦቹ በአካባቢው የሚደረገውን ተቃዎሞ በማደራጀት በኩል እጃቸው አለበት በሚል እንዳሰራቸው፣ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ድርጅት የደቡብ ክልል ዋና አደራጅ አቶ ዱባለ ገበየሁ መግለጻቸው ይታወሳል።

አቶ ዱባለ በክልሉ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር እርሳቸው የኢህአዴግ አባል በነበሩበት ጊዜ በተለይም የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት እና  የደኢህዴግ የፖለቲካ ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት አቶ አለማየሁ አሰፋ ቤተሰቦቹን እያሾመ ነው በማለት ገምግመዋቸው እንደነበርና አሁን የሚደርስባቸው ነገርም የዚያ በቀል መሆኑን ገልጸዋል።

በማረቃ ወረዳ በማሪ አካባቢ ሰሞኑን በተነሳው የሕዝብ አመጽ ሕዝቡ በፖሊስ ላይ እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል።

ዋካ የኔሰው ገብሬ ዲሞክራሲና ፍትህ በሌለበት ሁኔታ መኖር አልፈልግም በማለት ራሱን በእሳት አቃጥሎ ያጠፋበት ከተማ መሆኑ ይታወቃል።