አቶ ዓባይ ጸሃዬ የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች በሕዝብ ብዛትና በመሬት ስፋት ቀመር ከሚሰራ ኢህአዴግ ቢፈርስ እንደሚመርጡ አስታወቁ
(ኢሳት ዜና የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ/ም) የብአዴንና የኦህዴድ አመራሮች የፌደራል መንግስት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በሕዝብ ብዛትና በመሬት ስፋት ቀመር መሰረት እንዲሰሩ የሚያቀርቡትን ሃሳብ ውድቅ ያደረጉት አቶ አባይ፣ እንዲህ አይነት አሰራር ተግባራዊ ከሚሆን ኢህአዴግ ቢፈርስ እንደሚመርጡ ተናግረዋል።
አቶ ዓባይ ጸሃዬ የብአዴንና ኦህዴድ አመራሮች፣ የቢሮ አመራሮች፣ ምክትል አመራሮችና ምሁራን የባቡር፣ የመንገድ፣ የዩኒቨርሲቲዎች ስርጭት ከሕዝብ ብዛት አንጻር ፍትሃዊ ክፍፍል እንዲደረግ መጠየቃቸውን ይገልጻሉ። ”በትግራይ ትንሽ ቁጥር ላለው ሕዝብ ሶስት ዩኒቨርሲቲዎች ለምን ተሰራ? የሚሉና መንገዶችን በኪሎ ሜትር በመለካት የሚቃወሙ አሉ አሉት አቶ አባይ፣ አንዱ በሕዝብ ብዛት ይሰራ ይላል፣ ሌላው በመሬት ስፋት ቀመር ይሰራ የሚሉ አስተያየቶችን እንደሚሰጡ ተናግረዋል። “ይህን ዓይነት ጣያቄዎችን በውስጣቸው የያዙ ፓርቲዎችን ይዘን፣ ልዩነት ይዘን ደህና ነን የሚባል ነገር የለም” ያሉት አቶ አባይ፣ “የፌደራል ፕሮጀክቶችን በሕዝብ ብዛት መቼም አንሰራም። የድርቅ ራሽን አይደለም፣ ብስኩት አይደለም የምናድለው። የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች በሕዝብ ብዛትና በመሬት ስፋት ቀመር ከሚሰራ ኢህአዴግ ቢፈርስ መርጣለሁ።” ሲሉ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል።
በመከላከያ ሰራዊት ጄኔራሎች ሹመት ቀመርን አስመልክቶም አቶ ዓባይ ሲናገሩ፣ ”የከፍተኛ ወታደራዊ ሹመቶች ከሚገባው በላይ ተሰርቷል። ሰባት ወይም ስምንት ጄኔራሎች ብቻ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ከሽግግር መንግስት በኋላ የደቡብና የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ አንድ ክፍለጦር ያልመሩትን ጄኔራል አድርገን ሹመናል። ጄኔራሎችን ቁጥር አስመልክቶ ሂሳብ እየሰሩ መዋል ምን ይጠቅማል? አሜሪካና አውሮፓ ሙሉ ጄኔራሎች ለማፍራት ከ30 ዓመታት በላይ ይፈጅባቸዋል። እኛ ግን በ20 ዓመታት ውስጥ አፍርተናል።” በማለት የወታደራዊ ሹመቶች ፍትሃዊ ነው ብለዋል።