አቶ ኤርምያስ አመልጋ በዋስ እንዲፈቱ ትእዛዝ ተላለፈ

መጋቢት ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአክሰስ ሪል ስቴት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርምያስ አመልጋ ከቤት ግንባታ ጋር በተያያዘ ደንበኞቻቸውን አጭበርብረዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው እንዲታሰሩ ከተደረገ በሁዋላ፣ ፖሊስ የተለያዩ የጊዜ ቀጠሮዎችን ሲጠይቅ ቆይቷል። የከፍተኛው ፍርድ ቤት አራዳ ችሎት በተከሳሹ ላይ አቃቢ ህግ ተደጋጋሚ የምርምራ ጊዜ ሲጠይቅ በመቆየቱ ከዚህ በሁዋላ ተጨማሪ ጊዜ መስጠት ተገቢ አይደለም በሚል፣ አቶ ኤርምያስ 500 ሺ ብር አስይዘው እንዲፈቱ ወስኗል። የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ አቶ ኤርምያስ ይፈቱ አይፈቱ የታወቀ ነገር የለም። ፖሊስ ግን በውሳኔው ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።
አቶ ኤርምያስ ጫናው ሲበዛባቸው ወደ አሜሪካ ተመልሰው የነበረ ቢሆንም፣ መንግስት እንደማይታሰሩ ዋስትና መስጠቱን ተከትሎ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ይሁን እንጅ መንግስት ቃሉን በማጠፍ ግለሰቡ እንዲታሰሩና ምርመራ እንዲካሄድባቸው በመወሰኑ፣ ባለሃብቱ ለእስር ታዳርገዋል።